
ሰቆጣ: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እናቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ በየጊዜው በማድረግ የማህጸን በር ካንሰርን ቀድመው መከላከል እና ከተከሰተም ቫይረሱ ወደ ካንሰርነት ሳይቀየር በሕክምና ሊድኑ እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የማህጸን በር ካንሰርን ቀድሞ ለመከላከል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሦስት ሆስፒታሎች እና በሁሉም ወረዳዎች በዘመቻ መልኩ ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ አሰፋ ነጋሽ ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ክትባቱ በቤት ለቤት እና በትምህርት ቤቶች ከዘጠኝ ዓመት እስከ 14 ዓመት ያሉ ከ88 ሺህ በላይ ልጃገረዶችን በዘመቻ ለመከተብ እየተሠራ እንደኾነ ጠቅሰዋል።
ክትባቱን በመውሰድ ጤንነታቸው የተጠበቁ እናቶች እንዲኖሩ ለማድረግ በጤና ተቋማት እና በጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ አቶ አሰፋ ማኅበረሰቡም ለክትባቱ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ነው ያሳሰቡት።
ክትባቱን ሲከተቡ ያገኘናቸው ሴት ተማሪዎችም የማህጸን በር ካንሰር ክትባት ተጠቃሚ በመኾናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ተማሪ ኽምራዊት ዳንኤል የ8ኛ ክፍል ተማሪ ስትኾን የክትባቱ ተጠቃሚ በመኾኗ መደሰቷን ገልጻ ሌሎች ተማሪዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ አሳስባለች።
የማህጸን በር ካንሰር ሴቶችን የሚያጠቃ እና አስከፊ በሽታ እንደኾነ መገንዘቧን የገለጸችው ተማሪ እሌኒ ጣምተው ክትባት መውሰዷ ለወደፊት ለሚኖራት ሕይዎት ዋስትና እንደሚሰጣት እንደምታስብ ነው የተናገረችው።
አንዳንድ ተማሪዎች ክትባቱን በመፍራት ሳይከተቡ ይቀራሉ ያለችው ተማሪ እሌኒ በሽታው ተከስቶ ከመቸገር ቀድሞ መከላከል ይገባል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
የማህጸን በር ካንሰር የክትባት ዘመቻው በትምህርት ቤቶች እና ቤት ለቤት እንዲሁም በሆስፒታል ደረጃ እየተሰጠ የሚገኝ ሲኾን እስከ ኅዳር 13/2017 ዓ.ም ድረስ የክትባት ዘመቻው እንደሚቀጥል ከጤና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
