
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርም ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ እና ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ወርቁ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ ማኅበራት ለዝቅተኛው የኅብረሰብ ክፍል አገልግሎት እየሰጡ ነው።
ማኅበራቱ የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት በሀገር ልማት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ዓላማ ተደርጎ ቢቋቋሙም አሠራራቸው እና አደረጃጀታቸው ከተለምዷዊ የተላቀቁ ባለመኾኑ ዘይት እና ስኳር ከመሸጥ ያለፈ ሥራ እየሠሩ አለመኾኑን ገልጸዋል።
ማኅበራቱ ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ ተዋናይ እንዲኾኑ ማሻሻያ መደረጉን ነው ኀላፊው የገለጹት። ማሻሻያው ማኅበራቱ በቴክኖሎጂ ጭምር በመደራጀት ዘላቂ፣ ፈጣን እና ችግር ፈች አገልግሎት እንዲሰጡ ዓላማ ያደረገ ነው።
የማኅበራትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ አስፈላጊ ኾነው ያልተገኙ ማኅበራትን በማፍረስ፣ የተበታተኑትን ደግሞ ወደ አንድ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የፈለገ ዓባይ ዩኒዬን ሰብሳቢ ቻለው አላምኔ እንዳሉት ማሻሻያው የገንዘብ እጥረት እና የአሠራር ድክመት ያለባቸውን ማኅበራት በማቀናጀት ተቀራራቢ የኾነ ሥራ እንዲሠሩ አቅም ይፈጥራል። አሠራሩን በቴክኖሎጅ ለማጠናከር እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የልደታ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሰብሳቢ ውብእርስት እንዳለው እንዳሉት ደግሞ ማኅበራት የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት ዓላማ ተደርጎ ቢቋቋሙም በኢኮኖሚ፣ በመሥሪያ ቦታ ችግሮች እና ከኋላቀር አሠራር የተላቀቁ ባለመኾናቸው ዓላማቸውን እንዳያሳኩ አድርጓቸዋል። ሪፎርሙ ማኅበራትን በማሰባሰብ የሚታዩ ችግሮችን እንደሚፈታም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
