
ደሴ: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር የ2017 ዓ.ም የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብርን አስጀምሯል። በደሴ ከተማ በ2016 ዓ.ም 7ሺህ ለሚኾኑ ተማሪዎች ምገባ ተካሂዷል ያሉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ ናቸው፡፡
መምሪያ ኀላፊው በ2017 ዓ.ም 16 ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት። በአሁኑ ወቅት 8ሺህ 800 ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ምገባው በደሴ ከተማ በሚገኙ በሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጀመሩን የገለጹት ኀላፊው ለዘላቂነቱ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
በ2017 ዓ.ም ለተማሪዎች ምገባ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን የገለጹት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው መንግሥት ሰው ተኮር የኾኑ ተግባራትን እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ የተማሪዎች ምገባም የዚህ ዕቅድ አንድ አካል ነው ብለዋል።
ተማሪዎች በምግብ እጥረት ምክንያት የተለያዩ ጉዳቶች እንደነበሩባቸው በትምህርት ቤቱ የግብረገብ መምህር ተስፋየ ከበደ እና መምህርት ጥሩ ወርቅ ዋለልኝ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
መምህራኑ የምገባ ፕሮግራሙ ከተጀመረ በኃላ ግን ችግሮች ተቀርፈው የተማሪዎች ትኩረት ትምህርታቸው ላይ ብቻ መኾኑን አንስተዋል።
በምገባ መርሐ ግብሩ የታቀፉ ተማሪዎች እየተደረገ ያለው ምገባ በትምህርታቸው እንዲበረቱ እንዳስቻላቸው ነው ያብራሩት፡፡
በደሴ ከተማ የመርሐ ጥበብ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ምገባውን ለሚያስተባብሩ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
