
ደሴ: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ፣ በሰሜን ምሥራቅ እዝ የ801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ሰጣርጌ፣ የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ከቧንቧ ውኃ እስከ ወሎ ባሕል አምባ እንደሚሠራ እና 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በኮሪደር ልማቱ የሚሠራው መንገድ አጠቃላይ ስፋት 46 ነጥብ 5 ሜትር መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡
የሚሠራው የኮሪደር ልማት 3 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው የመንገድ አካፋይ፣ 20 ሜትር ስፋት ያለው የአስፓልት መንገድ፣ 5 ሜትር የሚሰፋ የእግረኞች መንገድ፣ 3 ሜትር ስፋት ያለው የብስክሌት መጋለቢያን ጨምሮ አንፊ ቲያትር፣ የሕጻናት መዝናኛ፣ የባሕል ማዕከል፣ ኳስ ሜዳ፣ ድልድይና የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የመኪና ፓርኪንግ እና የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ግንባታን ያካተተ ስለመኾኑ ተብራርቷል፡፡
ለፕሮጀክቱ ወደ 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ አስረድተዋል፡፡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አሥተዳደሩ የከተማ ልማት እና መሠረተ ልማት መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ ቃሲም አበራ የኮሪደር ልማቱ ደሴ ከተማን ውብ፣ ጽዱ እና ለነዋሪዎች የምትመች ከተማ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ልማቱ በከተማዋ ያለውን የመዝናኛ ችግር የሚያቃልል ፕሮጀክት መኾኑን የገለጹት አቶ ቃሲም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው የተናገሩት፡፡ በኮሪደር ልማቱ ከይዞታቸው ከተነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አቶ መስፍን መሐመድ እና ወይዘሮ ዓባይነሽ ካሳ በደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ መጀመር እንዳስደሰታቸው እና የይዞታ ቦታቸውን በፈቃደኝነት መልቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የቀበሌ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ተነሽዎች ደግሞ 100 ካሬ ሜትር ምትክ ቦታ እንደተሰጣቸው እና የግል ቤት ላላቸው የካሳ ክፍያ እንደተፈጸመም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
