የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 60 ዓመታት በአማካይ በ4 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር) ገለጹ።

75

አዲስ አበባ: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አፈጻጸም መገምገም እና በቀጣይ የባለድርሻ አካላት ሚናን መለየት የሚያስችል የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 60 ዓመታት በአማካይ በ4 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን እና ይህም ዝቅተኛ ኾኖ መመዝገቡን ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ ገልጸዋል።

የሀገሪቱ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢም ባለፉት 60 ዓመታት 1 ነጥብ 3 በመቶ ቢያድግም የሀገሪቱን የሕዝብ ቁጥር ጭማሬ የሚመጥን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ አለመቻሉን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 2 በመቶ እንዲያድግ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ 10 ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መኾኗን አንስተዋል።

ከሦስት አስርት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገር እንደምትኾን ዓለም ባንክን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ተቋማት መተንበዩንም ዶክተር ፍፁም አሰፋ አንስተዋል።

ሚኒስትሯ አጠቃላይ ያለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገት፣ ያደጉት ሀገራት ተሞክሮ፣ በሚቀጥሉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የት እንደሚደርስ እና የባለ ድርሻ አካላት ሚናን በተመለከተ ለውይይቱ መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱን ጨምሮ የግሉ እና የፍይናንስ ዘርፉ አንቀሳቃሾች ተሳታፊ ናቸው።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጽዱ እና ውብ ከተማን መገንባት የሁሉም ማኅበረሰብ ክፍል ኀላፊነት ነው።
Next articleለደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት የይዞታ ቦታቸውን በደስታ መልቀቃቸውን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡