
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በደብረ ማርቆስ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል። ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የብልጽግና ፓርቲን የ5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የጽዳት ዘመቻ አከናውኗል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፓርቲውን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ነው የጽዳት ዘመቻ ያደረገው። የአሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች የፓርቲው አባላት፣ በጎፈቃደኛ ወጣቶች እና የከተማ ሴፍትኔት ተጠቃሚ የማኅበረሰብ ከፍሎች የተሳተፉበት የጽዳት ዘመቻ አካሂዷል።
በጽዳት ዘመቻው ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፓለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አበባው ግዛቸው ጽዱ እና ውብ ከተማን መገንባት የሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ኀላፊነት መኾኑን ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን በማጽናት ሀገራዊ አንድነትን መገንባት እንደሚገባም ኀላፊው ገልጸዋል።
የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እና ለኑሮ ምቹ አካባቢን መፍጠር እንደሚገባ የገለጹት በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉ በከተማ አሥተዳደሩ የሴፍትኔት ተጠቃሚ የማኅበረሰብ ክፍሎች የልማት ሥራዎች እየተሳተፉ ራሳቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ ከከተማ ጽዳት እና ውበት ባለፈ የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
ማኅበረሰቡ ወደ ቀደመ ሰላሙ ተመልሶ በልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲኾን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
