
የአማራ ክልል የልዩ ኃይልና አድማ ብተና አባላት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ሂደት ጉልህ አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።
በምክትል ርእሰ መሥተደድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) የሚመራ ልዑክ በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ የልዩ ኃይልና አድማ ብተና የሠራዊት አባላት ጋር የትንሳኤ በዓልን አክብሯል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ የልዩ ኃይልና የአድማ ብተና አባላቱ ከመደበኛ ሠላምና ደኅንነትን ሥራው ጎን ለጎን የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ እንደክልል እየተሠራ ባለው የመከላከል ተግባር ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፤ እየተወጡ ላለው በጎ ተግባርም አመሥግነዋል።
የክልሉ ሠላምና የኅዝብ ደኅንነት ግንባቴ ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ደግሞ የልዩ ኃይልና አድማ ብተና አባላቱ በሽታውን ለመከላከል ያሳዩት ተነሳሽነት አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል። ሠራዊቱ የትንሳኤ በዓልን በመተሳሰብና አብሮነት እንዲያከብር ከመደበኛው በጀት ውጭ ከ400 ሺህ ብር በላይ መመደቡንም አስተውቀዋል። በዞንና በየደረጃው የሚገኙ አባላትም በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ተመሳሳይ ሥራ መሠራቱን ነው ያስታወቁት። በቀጣይም የክልሉ የፀጥታ መዋቅር እራሱን ከቫይረሱ በመጠበቅ ሕዝቡም በበሽታው እንዳይጠቃ መሥራት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።
የአንደኛ ብርጌድ አድማ ብተና ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር በቀለ ዓይቸው የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች አብረው በማሳለፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የፀጥታ ኃይሉ የበለጠ እንዲነቃቃና ሙያውን እንዲወጣ እንደሚያደርገውም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ