
አዲስ አበባ: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በጥራጥሬ፣ በቅባት እህሎች እና በቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አካሂዷል።
በጉባኤው ከ25 በላይ የውጭ ሀገራት እና ከ500 በላይ የሀገር ውስጥ የምርት ላኪዎች እና ገዥዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ኮንፈረንሱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እና የዓለም ንግድ ድርጅት ይዞት ለሚመጣው ተወዳዳሪነት የሀገሪቱ ላኪዎች ብቁ ኾነው እንዲገኙ የሚያስችል እና ልምድ የሚቀስሙበት መኾኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጥራጥሬ፣ በቅባት እህል እና ቅመማ ቅመም ዘርፍ በወጭ ንግድ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች መኾኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኤዳዎ አብዲ ኮንፈረንሱ የሀገር ውስጥ እና እና ዓለም አቀፍ ላኪዎችን እና ገዥዎችን በአንድ በማሠባሠብ ነባር የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር እና አዳዲስ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የፀጥታ ችግር፣ የምርት ክምችት፣ የምርት ማሸጊያ ጥራት ጉድለት፣ የውል እና ኢንቨስትመንት እርሻ አተገባበር ክፍተቶች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ንግድ ላይ ማነቆ መኾኑንም አንሰተዋል።
በርካታ የተለያዩ ሀገራት ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ በጥራጥሬ፣ በቅባት እህሎች እና በሌሎች ኤክስፖርት ተኮር ምርቶች ላይ በትብብር እና በጋራ ለመሥራት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መኾኗንም አንስተዋል።
በሀገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም በዘርፉ ላይ የሚታዩ የጥራት እና የዋጋ ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚያግዝ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
