
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤት 4ኛው ዙር ምርጫ 12ኛው ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛው መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ አዲስ ትርፌ እንዳሉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በችግር ውስጥ ኾኖም የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ከሥራዎቹ አንዱ ግዙፉ የዓባይ ድልድይ ይጠቀሳል ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትኾንም የ5ጂ ኢንተርኔት ተሟልቶላታል ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤ አዲስ ትርፌ የከተማዋ መሬት ጦም እንዳያድርም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በከተማዋ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ምክትል አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።
የከንቲባ ችሎትም በርካታ ጉዳዮችን የፈታ እና በመፍታት ላይ መኾኑንም ገልጸዋል።
በኑሮ ውድነት አየተሰቃየ ያለውን ማኀበረሰብ ከችግሩ ለማላቀቅ ለከተማዋ ነዋሪዎች የምግብ ፍጆታ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ 60 ሚሊዮን ብር ቢመደብም ችግሩን ማቃለል አልተቻለም ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
