
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር የኮሪደር ልማት በታቀደና በተደራጀ ሁኔታ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ሲሠራ ቆይቶ የተግባር ሥራው የማስጀመሪያ መርሀ ግብር በይፋ ዛሬ ተጀምሯል። የኮሪደር ልማቱ ከቧንቧ ውሀ እስከ ወሎ ባሕል አምባ የሚደርስ ሥራ መሆኑ ተገልፆል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቃሲም አበራ በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 46 ነጥብ 8 ሜትር መንገዱን ጨምሮ ስፋት ያለው ነው ብለዋል።
የመንገድ ሥራውን የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ፣ ከመንገድ ሥራው ውጭ ያለውን ልማት የደሴ ከተማ መንገድ ባለሥልጣን እና የደሴ” ዕድገት ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ” እንደሚሠሩት አቶ ቃሲም አበራ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ተጀምሮ በሌሎች ከተሞችም እንዲሰፋ የተቀመጠ ዋና ተግባር መሆኑ ይታወቃል። ደሴ ከተማ ለነዋሪዎቿ ሳቢ ፣ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ አንዱ ተግባር ይህ በመሆኑ በመንግሥት ፣ በከተማችን ነዋሪዎች ፣ በሀገራችንና በክልላችን ባለሀብቶች ተሳትፎ ፋይናንስ አድራጊነት በታቀደው ጊዜና ጥራት መሰረት ከፋተኛ ክትትልና ድጋፋ የሚሠራ መሆኑን የደሴ ከተማ ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገልፀዋል።
አቶ ሳሙኤል ይህን ትውልድ ተሻጋሪ ፣ ለሰው ፤ በሰው የሆነ ተግባር ሁሉን የከተማ ፍላጎት የሚያሟላ ዘመኑን የሚመጥን አስፈላጊ ሥራ ለመደገፋ ሁሉም የከተማችን ማኅበረሰብ እንደወትሮው ተባባሪ እንደሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
