
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን 125 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላለው የገለጎ ገንዳ ውኃ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መሳለጥ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ የዞኑ አሥተዳደር ገልጿል። የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ያለበትን ሁኔታ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራር አባላት ጉብኝት አካሂደዋል።
የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ አንዳርጌ ጌጡ በወቅቱ እንዳሉት፤ በፌዴራል መንግሥት በጀት እየተከናወነ ያለው የገለጎ ገንዳ ውኃ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት የሕዝቡን የቆየ የመንገድ ግንባታ ጥያቄ የሚመልስ ነው። መንገዱ ለኢንዱስትሪና ለውጭ ምንዛሬ የሚውሉ ሰብሎችን የሚያመርቱ ቋራና መተማ ወረዳን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና ከመሬት ይዞታ ጋር የሚነሱ ጉዳዮችን በመፍታት የመደገፍ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል። የዞኑ መንገድ መምሪያ ኃላፊ ዓባይነህ ወረታ በበኩላቸው፤ ከገለጎ ገንዳ ውኃ ከተማ የሚሠራው መንገድ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ ነው።
አካባቢው ከፍተኛ ሃብት ያለበት ቢሆንም የመንገዱ ያለመስተካከል ችግር ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የመንገዱ መገንባት ያለውን ሃብት አልምቶ ለመጠቀምና የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳደግ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የቻይና መንገድ ተቋራጭ “ዜሲሲሲ” ተቆጣጣሪ መሀንዲስ አቶ ብርሃኑ ጌታ፤ 125 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ይሄው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን የመሬት ቆረጣና ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአካባቢው ማኅበረሰብና አሥተዳደሩ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በጉብኝቱ የዞኑ የሥራ ኀላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!