
ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ከገለጉ እስከ ገንዳ ውኃ እየተሠራ ያለውን የአስፋልት መንገድ የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች ጎብኝተውታል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ እንደገለጹት ዞኑ በተለይ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የግብርና ምርቶችን በማምረት የሚታወቅ ነው።
ስለኾነም የአስፋልት መንገዱ ሲጠናቀቅ ለአምራቾች፣ ለነጋዴዎች እና ለዞኑ ጠቅላላ ሕዝብ የጎላ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅም አለው ብለዋል። ለመንገድ ሥራው የነዳጅ እጥረት እንዳያጋጥም እና ሌሎች የፀጥታ ችግሮች እንዳይደርሱ ትብብር እና እገዛ እንደሚያደርጉ ነው አሥተዳዳሪው የጠቆሙት።
የዞኑ መንገድ መምሪያ ኀላፊ አባይነህ ወረታ እንደተናገሩት እየተሠራ ያለው የአስፓልት መንገድ ከገለጉ እስከ ገንዳ ውኃ 125 ኪሎ ሜትር ነው። የአስፋልት መንገዱም በታለመለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል። መንገዱ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ዞኑ የሰሊጥ አምራች በመኾኑ የንግድ ትስስሩን እና ማኅበራዊ ግንኙነቱን እንደሚያሳልጠው ኀላፊው አስረድተዋል።
ለሚሠራው የአስፋልት መንገድም የሦስተኛ ወገን ለሥራ ችግር እንዳይኾንም አስፈላጊውን እገዛ እና ክትትል እናደርጋለን ያሉት ደግሞ የመተማ ወረዳ አሥተዳዳሪ ደሳለኝ ሞገስ ናቸው።
የሳይት መሃንዲሱ ብርሃኑ ጌታ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ኾኖታል። ለአካባቢው ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተሠርቶ እንደሚጠናቀቅም አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!