
ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ9 እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ክትባቱ እንደሚሰጥ በጤና ሚኒስቴር የክትባት ክፍል አማካሪ ዮሃንስ ላቀው ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚኾኑት በአማራ ክልል ለሚገኙ ልጃገረዶች የሚሰጥ ነው።
አማካሪው እንዳሉት ኢትዮጵያ የማህጸን በር ካንሰርን አስመልክቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እየሠራች ትገኛለች። ግቡን ለማሳካት ከግብረ ስጋ ግንኙነት በፊት ክትባቱን በመስጠት፣ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ እና በሽታው ከተገኘ ደግሞ ማከም ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ይገኝ የነበረው ክትባት ዝቅተኛ ስለነበር ክትባቱ ይሰጥ የነበረው ለ14 ዓመት ልጃገረዶች ብቻ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት በቂ ክትባት በመገኘቱ ከ9 እሰከ 14 ዓመት ለሚገኙ ልጃገረዶች መስጠት አስፈልጓል ነው ያሉት።
በቂ ግብዓትም ወደ ክልሉ የማድረስ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ክትባቱ በተሳካ መንገድ እንዲሰጥ የጤና ባለሙያዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ወላጆች እና የሃይማኖት አባቶች እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓመት ከ8 ሺህ በላይ እናቶች በማህጸን በር ካንሠር በሽታ ይሞታሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!