1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ልጃ ገረዶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

31

ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማህጸን በር ጫፍ ካንሠር ማህጸን ላይ የሚከሰት እና ያልተለመደ የሰውነት ህዋሳት መብዛት ነው። ካንሰር በሰውነት ውስጥ ያሉ ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ በኾነ መልኩ በማደግ ወደ ሌላው የሰውነት ክፍሎች ሲሰራጩ የሚከሰት በሽታ እንደኾነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች ከጡት ካንስር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የማህጸን በር ጫፍ ካንሠር በሽታ በቫይረስ የሚከሰት በሽታ ነው። በለጋ ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኑነት መጀመር፣ ከብዙ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም፣ በአባላዘር በሽታ መጠቃት፣ የሰውነት በሽታ መከላከል አቅም መዳከም እና ሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ለበሽታው መነሻ እንደ መንስዔ ኾነው ተቀምጠዋል።

በበሽታው የተያዙ ሴቶች ደግሞ ያልተለመደ የደም መፍሰስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ያልተለመደ መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ የእግር ማበጥ፣ የኩላሊት በሽታ እዲሁም ሽንት እና ሰገራ ላይ ደም መቀላቀል የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ። አንድ ለአንድ በመወሰን፣ በለጋ ዕድሜ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በመታቀብ፣ በመደበኛ የማህጸን ምርመራ እና በክትባት በሽታውን መከላከል ይቻላል።

በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በሽታውን ለመከላከል ሲሠራ መቆየቱን የክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው ገልጸዋል። ከመከላከያዎቹ ውስጥ ደግሞ ክትባት አንዱ ነው። ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት የሚገኙ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት እንዲያገኙ ቢወሰንም ክትባቱ ውድ በመኾኑ በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመታት መከተብ የተቻለው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሴቶችን ብቻ ነው።

በዚህ ዓመት በቂ የክትባት መድኃኒት በመገኘቱ ከ9 እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ልጃ ገረዶች ክትባት እንዲሰጥ ተደርጓል። ክትባቱ እስከ ኅዳር 13/2017 ዓ.ም የሚሰጥ ሲኾን “ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ልጃ ገረዶች ተደራሽ” ይኾናል። ክትባቱ በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች በዘመቻ ይሰጣል።

ዳይሬክተሩ የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር ከሌሎች ካንሰሮች የሚለየው ቀድሞ በመለየት ማከም መቻሉ እና ክትባት የተዘጋጀለት መኾኑ ነው። ክትባቱ በሌሎች ሀገራት በዕድሚያቸው ከፍ ላሉ ሴቶች እና ወንዶች ጭምር የሚሰጥ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የማኅጸን ጫፍ በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ ፍሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።
Next articleየማህጸን በር ካንሰር ክትባት በተሳካ መንገድ እንዲሰጥ ማኅበረሰቡ እንዲተባበር ጥሪ ቀረበ፡፡