
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም( አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኝ የዶሮ ርባታ ማዕከልን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ሚኒስትሮች፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተጎበኘው የደብረ ሆላንድ የደሮ ርባታ ማዕከል ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የደሮ እርባታ ማዕከሉ በ144 ሚሊዮን ብር በ2012 ዓ.ም መቋቋሙን ተናግሯል። ፕሮጄክቱ በቀን 120 ሺህ ጫጩቶችን ያመርታል ተብሎ መቋቋሙን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አኹን ላይ ከ50 ሺህ በላይ እንቁላል በቀን እንደሚያመርት ተናግረዋል። እንቁላል ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ መኾኑንም ገልጸዋል። እንደ ሀገር ለተጀመረው የሌማት ትሩፋት ማሳያ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ እምቅ የእንስሳት ሃብት እንዳለውም ገልጸዋል። በከተማዋ በእንስሳት ርባታ የሚያለሙ ባለሀብቶች እና ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውንም አመላክተዋል። የደብረ ሆላንድ የድሮ እርባታ ማዕከልም ደሮ ለአካባቢው እና ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ መኾኑን ነው የተናገሩት። በፕሮጄክቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተካሄደበት መኾኑንም ተናግረዋል። በተለይም ለተደራጁ ወጣቶች ልምድ የሚሰጥ እና በዘርፉ እንዲሠማሩ የሚያበረታታ ነውም ብለዋል።
በከተማዋ ከ650 በላይ የአማራች ዘርፎች ተመልምለው በግንባታ እና በምርት ሂደት ውስጥ መኾናቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በስፋት እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። በክልሉ የጸጥታ ችግር ኖሮም የኢንዱስትሪ ፍሰቱ እንደቀጠለ ነው ብለዋል። ለኢንዱስትሪው መጨመር የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላም ወዳድ መኾንና በከተማ አሥተዳደሩ የሚሰጠው ፈጣን አገልግሎት መጨመር መኾኑን ነው የተናገሩት።
ከባለሀብቶች ጋር የመወያየት ባሕል እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት። በዚህ ዓመትም በኢንዱስትሪው ዘርፍ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል። በሁሉም ዘርፍ ሰፊ እና አዳዲስ ፕሮጄክቶች እየመጡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ኢንዱስትሪ ሰላም እንደሚሻ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሰላሙ ፈተና ባይኖር ኖሮ አኹን ካለው የኢንዱስትሪ ፍሰት በላይ መሥራት ይቻል እንደነበር ነው የተናገሩት።
ከሰላሙ ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች መከናወቸውንም ገልጸዋል። ሰላሙን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች የኢንዱስትሪው ዘብ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!