
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያውያን ልማድ በአንድ ተላላፊ በሽታ ታምሞ ያገገመ ሰው ‘‘ተሸለመ፤ ወጣለት’’ ይባላል፤ በበሽታው አንዴ ተይዞ ያገገመ ሰው መልሶ በዚያ በሽታ እንደማይያዝ ይገለጻል፤ ይህንንም ሁኔታ ለመግለጽ ወረርሽኝ ወዳለበት አካባቢ እንዳንሄድ ሲነገረን ‘‘እኔኮ ተሸልሜያለሁ፤ ወጥቶልኛል’’ እንላለን፤ ለኮሮና ግን ይህ አይሠራም፡፡
በደቡብ ኮሪያ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች መልሰው በቫይረሱ እየተጠቁ ነው፡፡ የደቡብ ኮሪያ የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች እንደገለጹት 163 ከኮሮና ቫይረስ ሕመም ያገገሙ ሰዎች በድጋሜ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
የአገሪቱ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ታምመው ያገገሙና ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ የነበሩ ሰዎች መልሰው በቫይረሱ መያዛቸው እንቆቅልሽ እንደሆነበት አስታውቋል፡፡ በቻይናም መሰል ሁኔታዎች ማጋጠማቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህም ‘‘ሰዎቹ እንደ አዲስ ተይዘዋል ወይስ የምርመራ ውጤት ችግር ነበር?’’ የሚል ውዝግብ ፈጥሯል፡፡ የውዝግቡ መንስኤ ሰዎች አንድ ጊዜ በሆነ በሽታ ከተያዙና ካገገሙ ሰውነታቸው ያንን የበሽታ መንስኤ የመቋቋም ልምድ ስለሚያዳብር እንደሚቋቋሙት መታመኑ ነው፡፡ ከዚህ እሳቤ የተነሱ የዘርፉ ተመራማሪዎች ‘‘መጀመሪያውኑም ሰዎቹ ሙሉ በሙሉ ሳያገግሙ በተሳሳተ የምርመራ ውጤት ከቫይረሱ ነፃ ሆኑ ብለን እንጅ ድጋሜ አልተያዙም’’ እያሉ ነው፡፡
ሌሎች ደግሞ ‘‘ቫይረሱ ከዚህ ቀደም ከምናውቃቸው ቫይረሶች የተለየ ባሕሪ ስላለው ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ከቫይረሱ አገግመው የነበሩ ሰዎችም እንደገና ሊያዙ ይችላሉ ማለት ነው፤ መፍትሔም መጠንቀቅ ነው’’ እያሉ ነው፡፡ እውነታው ይህ ከሆነና በሽታው አንዴ የያዘውን ሰው መልሶ ከያዘ ደግሞ ክትባት ለማግኜት እየተሄደበት ያለውን የተለመደ መንገድ እንዳያረዝመው ያሰጋል፡፡
የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለማችን 2 ሚሊዮን 344 ሺህ 964 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 604 ሺህ 422 ሰዎች ከሕመሙ አገግመዋል፤ 161 ሺህ 191 ሰዎች ደግሞ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ምንጭ፡- ዩፒአይ
በአብርሃም በዕውቀት