“የወተት ምርታማነትን በማሳደግ የሌማት ትሩፋትን ማሳካት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው” የጎፋ ዞን

47

አዲስ አበባ: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጎፋ ዞን በወተት እና በስጋ ያለው አቅም ትልቅ ነው ሲሉ የዞኑ አሥተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ ተናግረዋል። ጌታቸው ዘውዴ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ አርሶ አደር ናቸው። ከዚህ በፊት የሀገር ውስጥ ዝርያ ያላቸውን ላሞች ብቻ በማርባት አነስተኛ የውተት ምርት ያገኙ እንደ ነበር ያስታውሳሉ።

በሰባት ከብቶች አንድ የተሻለ ዝርያ ያላት ላም በመቀየር በቀን እስከ 12 ሊትር ወተት እንደሚያልቡ ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜም አርሶ አደሩ የተሻሉ ላሞችን ብዛት 14 አድርሰዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በቅርበት ወደሚገኝ የወረዳ ከተማ ለማድረስ የእቃ እና የትራንስፖርት ችግር እያጋጠማቸው በመኾኑ ብዛት ያለው ወተት እየተበላሸባቸው መኾኑን ተናግረዋል።

በገዜ ጎፋ ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ኀላፊ አሸናፊ ገዛኸኝ በወረዳው 84 የወተት መንደሮች እንደሚገኙ ገልጸው ወደ ሥራ የገቡት 11 ብቻ መኾናቸውን አብራርተዋል። ከ11 ሺህ በላይ በወተት ርባታ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በወረዳው ይገኛሉ ያሉት ኀላፊው በቀን ከአንድ ላም በአማካይ 14 ነጥብ 6 ሊትር ወተት እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የዞኑ አሥተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ ዞኑ በወተት እና ስጋ ያለው አቅም ትልቅ ነው ብለዋል። በስጋ በአንድ ገበያ ብቻ 40 መኪና ድረስ የስጋ ከብቶች ለገበያ ይቀርባሉ ብለዋል። ይሁን እና የተሻሉ ዝርያዎች እና ጥራት ያለው የስጋ ምርት እንዲቀርብ ከአርሶ አደሮች ጋር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በገዜ ጎፋ ወረዳ የአርሶ አደሮችን ችግር ለማቃለል በወረዳው በባለሃብቶች እና ራሳቸው አርሶ አደሮችን በማኅበር በማደራጀት የወተት ማቀነባበሪያ እንዲኖራቸው እየተሠራ ይገኛል ብለዋል አሥተዳዳሪው። እስከ አሁንም የአንድ ማቀነባበሪያ ማሽን ግዥ አልቆ ወደ ወረዳው ገብቷል፤ ሁለተኛው በዞኑ እገዛ በቅርቡ ግዥ ይፈጸማል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዐይን ሞራ ግርዶሽ ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና እንዲመጡ ኅብረተሰቡ ርብርብ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡
Next articleበደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ ፍሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።