የዐይን ሞራ ግርዶሽ ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና እንዲመጡ ኅብረተሰቡ ርብርብ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡

35

ባሕርዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ እንደመጡ የተናገሩት የ64 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው አቶ ላቀ መሀሪ ዐይናቸው በመጎዳቱ እርሻ ለማረስ ተቸግረው መቆየታቸውን ገልጸው አሁን በተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና የዐይናቸው ብርሃን መመለሱን ገልጸውልናል፡፡

ከሰዴ ጊወርጊስ የመጡት ወይዘሮ የግዴ ምስክር ዐይናቸው ተጎድቶ መቆየቱን ነግረውናል፡፡ ወይዘሮ የግዴ ልጅ ስላልነበራቸው መሪም ጧሪም አጥተው ሲቸገሩ እንደቆዩ ነው ያስረዱት፡፡ ዛሬ ሕክምና አግኝተው የዐይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

መምህር ይድነቃቸው ደባስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ዐይናቸው ማየት ተስኖት ለማስተማርም ኾነ ሌሎች ጉዳዮቹን ለመከወን በጣም ተቸግረው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ መምህሩ አሁን በተደረገው የዐይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና ሙሉ በሙሉ ማየት መቻላቸው እንዳስደሰታቸው ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

የፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዐይን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኪሩቤል ኤፍሬም የዐይን ሞራ ግርዶሽ በአብዛኛው በዕድሜ መግፋት እንደሚከሰት ገልጸዋል፡፡ በዕድሜ ምክንያት ዕይታቸው የሚቀንስ ሰዎችን ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው በሚል ብዙዎች ከቤት ውስጥ እንዲውሉ እየተደረጉ እንደኾነም ነው ያብራሩት፡፡

እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸውን ሰዎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በክልሉ ተንቀሳቅሶ ወደ ሕክምና መጥተው እንዲረዱ እያደረገ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የዐይን ሞራ ግርዶሽ መታከም የሚችል ነገር ግን በዓለም ደረጃ ዕይታን ከሚያጠፉ ምክንያቶች ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀመጥ ስለመኾኑም ነው ያስረዱት፡፡

ኅብረተሰቡ ይህንን በመገንዘብ ዕድሜያቸው ከፍ ብሎ ዕይታቸው የቀነሱ ሰዎች በዘመቻው በመሳተፍ የዕድሉ ተጠቃሚ መኾን እንዲችሉ እርብርብ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ በፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዐይን ሕክምና አስተባባሪ እና የኪዩር ብላይንድነስ ተወካይ ተስፋለም ግዛቸው
በዚህ ዙር ሕክምና 566 ሰዎችን የዐይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ጥገና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ያለባቸው ከ800 በላይ ሰዎች በተለያዩ ወረዳዎች እንደተለዩ እና ሕክምና ለመስጠት እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ በመጀመሪያው ቀን ሕክምናም 176 ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ ስለመቻሉ አንስተዋል፡፡ በየቀኑ ከዚህ ከፍ ያለ ቁጥር ለማስተናገድ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡

ልየታ ተደርጎላቸው ከየትኛውም አካባቢ ለሚመጡ ታካሚዎች ወጫቸው ተሸፍኖ ሕክምናው እንደሚሰጣቸውም ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ሕክምና ከዘመቻ ሥራው ውጭ ባለፈ ለአንድ ታካሚ እስከ 10 ሺህ ብር ወጭ ሊጠይቅ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

ይህ ዘመቻ ከኅዳር 08/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ኅዳር 12/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ የተናገሩት አስተባባሪው ወደፊትም በክልሉ ባሉ ዞን እና ወረዳዎች የልየታ ሥራ በመሥራት ቀጣይነት ያለው ሕክምና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች ታላቁን ሕዳሴ ግድብ ጎበኙ።
Next article“የወተት ምርታማነትን በማሳደግ የሌማት ትሩፋትን ማሳካት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው” የጎፋ ዞን