
አዲስ አበባ: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢንተርፕርነርሺፕ ለሁሉም” በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በመድረኩ የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን (ዶ.ር) ለበርካታ ወጣቶች የተለያዩ የክህሎት ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን እና ለሥራ ፈጣሪዎች የተለያዩ ዕድሎችን በማመቻቸት ሥራ ፈጠራ እንዲያድግ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የተለወጠች፣ በሥራ ፈጠራ የተሻለች ሀገር እና በሥራ ፈጠራ ላይ የተመሠረተ ትውልድ ለመፍጠር ያስችል ዘንድ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦች መበረታታት እንዳለባቸው ከአደጉት ሀገራት መማር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዶክተር በለጠ ሞላ ለሥራ የተመቼ ሥነ ምህዳር መፍጠር እና በሥራ ፈጠራ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ሽግግር እንዲኖር ለማስቻል ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት እና ምቹ የኾነ የፖሊሲ ማዕቀፍ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት። የኢንተርፕርነርሺፕ ባሕል እየጎለበተ እንዲሄድም ዘርፉን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሀት ካሚል ኢንተርፕርነርሺፕ የውስጥ አቅምን ለማነሳሳት እና ለመጠቀም እንዲኹም ከዓለም ጋር ለመተሳሰር እጅጉን ጠቃሚ መኾኑን አይተናል ብለዋል።
ሚኒስትሯ ሙፈሪሀት ካሚል በዘርፉ ከሌሎች የዓለም ሀገራት የሚወሰድ ብዙ ነገር በመኖሩ ኢንተርፕርነርሺፕ በሳምንት ብቻ ተከብሮ የሚተው ሳይኾን ዓመቱን ሙሉ የሚሠራበት ዘርፍ መኾን አለበት ነው ያሉት።
በባለፉት ሁለት ዓመታት ኢንተርፕርነርሺፕን ከኅዳር እስከ ኅዳር በሚል ንቅናቄ ብዙ ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት ለብዙ የሥራ ፈጣሪዎች የስኬት መንገድ መክፈት መቻሉንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!