
አዲስ አበባ: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ምክር ቤት አሥተባባሪነት የንግድ አውደ ርዕይ እና ባዛር ተከፍቷል። በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ኅዳር 29 ቀንን ስናከብር የሀገራችን ሕገ መንግሥት የጸደቀበት እና ኅብረ ብሄራዊ አንድነት እውን የኾነበት መኾኑን በማስታወስ ነው ብለዋል የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙዜና አልከድር።
ሕዝባዊ አንድነትን ከማረጋጥም አንጻር ይህ ቀን መከበሩ ሁለንተናዊ ፋይዳ አለውም ብለዋል። ዛሬ የምንከፍተው ባዛር እና አውደ ርዕይ ባሕሎቻችን ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ያላቸውን ፋይዳ ለማስገንዘብ ያለመ ነውም ብለዋል። የባሕል ወረራን ለመከላከል እና የሀገርን ጥበብ ለኢኮኖሚ ለማዋል በእጅጉ ይረዳልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!