የዓሳ ሃብት ልማቱ በመሠረተ ልማት ችግር እየተፈተነ ነው።

62

ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓሳ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም መንገድ፣ ኤሌክትሪክ እና መሰል የመሠረተ ልማት ግብዓቶችን በማሟላት ችግሩን ማቃለል እንደሚገባ የአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ገልጿል። የአማራ ክልል ለዓሳ ሃብት ልማት የሚውሉ በርካታ ሐይቆችን፣ ግድቦችን እና ወንዞችን የያዘ ክልል ነው። በክልሉ በእነዚህ ውኃማ አካባቢዎች ላይ ወጣቶችን በማደራጀት በዓሳ ማስገር ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ተደርጓል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አበርገሌ ወረዳ ከዚህ በፊት በዓሳ ማስገር፤ አሁን ላይ ደግሞ ከአምራቾች በመረከብ ለማኅበረሰቡ እያቀረበ የሚገኘው ሳረ ሰሎሞን አንዱ ነው። ወጣት ሳረ ለሰባት ዓመታት ያህል በተከዜ ግድብ ላይ ዓሳ በማስገር ለተረካቢዎች ሲያስረክብ ቆይቷል። አሁን ላይ ደግሞ በዓሳ ማስገር ባገኘው ጥሪት የራሱን ተሽከርካሪ በመግዛት ከአምራቾች በመረከብ ለነጋዴዎች ያስረክባል።

ይሁን እንጅ በአካባቢው በተከሰተው የሰላም እጦት ችግር እና በመንገዱ አስቸጋሪነት ምክንያት ተረካቢ ነጋዴዎች ወደ አካባቢው በተፈለገው ጊዜ ስለማይገቡ የተመረተው ዓሳ ብልሽት እያጋጠመው መኾኑን ገልጿል። የመብራት እና የመንገዱን ችግር መፍታት ከተቻለ የአካባቢው የዓሳ ሃብት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል እንደኾነ በተስፋ ይጠብቃል።

በጣና ሐይቅ በማኅበር ተደራጅተው ከሚሰሩት ውስጥ ያነጋገርነው ሌላኛው ወጣት እንዳለው ደግሞ ከዚህ በፊት ለዓሳ ልማቱ ትኩረት ባለመሠጠቱ ከምግብነት ያለፈ ሥራ መሥራት አልተቻለም። አሁን ላይ በማኅበር በመደራጀት ወደ ማስገር በመግባታቸው በየወሩ እስከ 40 ሺህ ብር የትርፍ ክፍፍል ያደርጋሉ።

የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት የመሥሪያ ቦታ፣ የማቀዝቀዣ እና ሌሎች ግብዓቶችን ድጋፍ ቢያደርግም የመንገድ፣ የመብራት መቆራረጥ እና ደረጃውን የጠበቀ ማስገሪያ መረብ እጥረት አሁንም ለዓሳ ሃብት ልማት ሥራው ፈተና መኾኑን ነግሮናል። የአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት አሥተባባሪ ሙሉቀን ዘሪሁን እንዳሉት ክልሉ በዓመት ከ40 ሺህ እስከ 70 ሺህ ቶን ዓሳ የማምረት አቅም አለው።

የክልሉን የዓሳ ሃብት በዘላቂነት ለማልማት እና ለመጠቀም ወጣቶች በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። እስከ አሁንም በክልሉ 960 ወጣቶች በ64 ማኅበራት ተደራጅተው ወደ ማምረት እንዲገቡ ተደርጓል። ጀነሬተር፣ ማቀዝቀዣ፣ የማስገሪያ መረቦችን እና ሌሎች ግብዓቶችን ለወጣቶች የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ለአብነት ያህል በ2016 ዓ.ም አንዱ ማኅበር 8 ሺህ 120 ኪሎ ግራም ዓሳ ለገበያ በማቅረብ 2 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል። የዓሳ ሃብት ልማቱን ለማስፋት ከውኃማ አካላት ባለፈ በጓሮ የዓሳ ግብርና ልማት ጭምር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የዓሳ ሃብት ልማቱን ለማስፋት በቴክኖሎጅ ጭምር በመታገዝ የዓሳ ጫጩት ማስፈልፈል ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ በፊት እስከ 500 ሺህ ጫጩት የማስፈልፈል አቅም የነበረውን ቴክኖሎጅ ወደ 3 ሚሊዮን መፈልፈል እንዲችል የማሻሻል ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።

የዓሳ ሃብት ልማቱን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ቢሠሩም አሁንም ያለወቅቱ ማስገር፣ ሕገ ወጥ ማስገሪያዎችን መጠቀም፣ የመንገድ እና የመብራት ችግር ባለባቸው እንደ ተከዜ በመሳሰሉ አካባቢዎች የሚመረተውን ዓሳ በወቅቱ ለተጠቃሚ ያለማድረስ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

የዓሳ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም መንገድ፣ ኤሌክትሪክ እና የመሳሰሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እና የማስገሪያ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት በመንግሥት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኾናቸውን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላም እና ልማታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
Next articleየሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ምርታማነት ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ልማትን ከግብ ለማድረስ እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገለጹ።