ሰላም እና ልማታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

37

ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የቃብትያ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ተመርቋል። በምረቃ ምነ ሥርዓቱ ያገኘናቸው ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሠራው ማሞ ሆስፒታሉ ከመገንባቱ በፊት ሆስፒታል ፍለጋ ሩቅ ቦታ ይሄዱ እንደነበር ጠቅሰዋል። በተለይ ሕጻናት የበለጠ ተጎጂ እንደነበሩ እና አሁን ላይ ችግሩ እንደሚቀረፍላቸው ተናግረዋል። አሁን ላይ ሆስፒታሉ በመገንባቱ እፎይ እንደሚሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ጤና ካለ ሌላውን እንደርስበታለን ነው ያሉት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሼህ የኑስ መሐመድ ለሕክምና ፍለጋ መተማ እና ጎንደር መሄድ እንደሚቀርላቸው ገልጸዋል። በግንባታውም ኅብረተሰቡ በጉልበቱ እና በገንዘቡ መርዳቱን ጠቅሰው በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ባለሃብቶች፣ ድርጅቶች እና መንግሥትም እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ ሰላም እና ልማታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የልቡ መሻት የኾነው የራሱ አሥተዳደር በመመሥረቱ እና በልጆቹ እየተመራ የዘመናት የማንነት እና የወሰን ጥያቄውን በላቡ እና በሕግ ለማጽናት በአንድ እጁ ሰላምን እና የሕግ የበላይነትን እያረጋገጠ በሌላኛው እጁ ደግሞ መሠረተ ልማቶችን እየገነባ ይገኛል ብለዋል።

በምጣኔ ሃብት የበለጸገች ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ጤናማ ትውልድ ያስፈልጋል። ለጤናማ ትውልድም ጥራት ያላቸው የጤና ተቋማትን ማስፋፋት ወሳኝ ነው። ስለኾነም በአንድ በኩል የጤና ተቋማትን መገንባት በሌላ በኩል በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት እና በዕውቀት የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ተቋማትን ማጠናከር እና ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በአማራ ልማት ማኅበር የሚገነባ የዕውቀት በር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መሠረት ድንጋይ መቀመጡ እና የቃብትያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መመረቁም ለልማት የተሰጠውን ትኩረት አመላካች ነውም ብለዋል አቶ አታላይ። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የማንነት ይከበርልኝ ጥያቄ ከዞኑ አልፎ በመላው አማራ መቀጣጠሉን አስታውሰዋል። ጥያቄውን ለማዳፈን ብዙ ግፍና በደል መፈጸሙንም ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ከዓመታት የጸና ተጋድሎ፤ ለእውነት እና ርትዕ ከተከፈለ መስዋዕትነት በኋላ ያገኘውን ነጻነት እያጣጣመ ሰላሙን እያስጠበቀ ነው። በሌላ በኩል ወኔ፣ እልህና ተስፋን የበጀት ምንጭ በማድረግ መሠረተ ልማቶችን እየሠራ አሻራውን ለታሪክ እያስቀመጠ ይገኛል ብለዋል አቶ አታላይ።

”የማንነት ትግላችን የራሳችን ዕድል በራስ የመወሰን ትግል ነው” ያሉት የቃብትያ ሁመራ ዋና አሥተዳዳሪ ትግላቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ኮሪደርን አስከብሮ የኢትዮጵያን ህልውና ከውጪ ተላላኪዎች የመጠበቅ ሀገራዊ ተልዕኮም መኾኑን ገልጸዋል። እኛ ከወላጆቻችን የወረስነውን ታሪክ የምናከብር እና የምናስቀጥል ነን፤ ወላጆቻችን ለዓመታት ያደረጉት ራስን የመኾን እሴት አክብረን እንሠራለን ብለዋል።

ማኅበረሰቡን በማስተባበር እና ባለን የውስጥ አቅም የልማት ሥራዎችን እያጠናቀቅን ለሕዝባችን ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እናደርጋለን ነው ያሉት። ፕሮጀክቱን ስንገነባ የተማርንበት ነገር ቢኖር ማኅበረሰብን በማሰለፍ፣ በቁርጠኝነት እና በእንችላለን መንፈስ ከተጀመረ የማይጠናቀቅ ነገር እንደሌለ ነው፤ በዚህም ከፕሮጀክቱ 11 ሕንፃዎች ውስጥ አራቱን አጠናቅቀናል ብለዋል።

በወረዳው ከጤና ጣቢያ ያለፈ የሕክምና ተቋም አልነበረም ያሉት አቶ አታላይ የተመረቀው የቃብቲያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልም በወረዳው የመጀመሪያ መኾኑን ነው የገለጹት። ይህም በወረዳው የጤና አገልግሎት ሽፋንን እንደሚያሳድግ ጠቅሰዋል።

በነበረው የሰላም እና የጸጥታ ፈተና ሳይበገሩ ጀምረው መጨረሳቸው ችግርን ተቋቁሞ የመሥራት አቅማቸውን እንዳጎለበተው ገልጸዋል። ከፕሮጀክቱ የተገኘው የሙያ እና ክህሎት ልምድ ለቀጣይም አቅም እንደሚኾን ተናግረዋል።

አቶ አታላይ ፕሮጀክቱ ስድስት ወር መውሰዱን፣ ለአራት የሕክምና ብሎኮች እና ሌሎችም ግንባታዎች 27 ሚሊዮን 617 ሺህ ብር መፍጀቱን ገልጸዋል። የሆስፒታል ግንባታውን ለማጠናቀቅ እገዛ ያደረጉ አካላትንም አመሥግነዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን የወደደ ሁሌም አሸናፊ ነው” አሸተ ደምለው
Next articleየዓሳ ሃብት ልማቱ በመሠረተ ልማት ችግር እየተፈተነ ነው።