“ሰላምን የወደደ ሁሌም አሸናፊ ነው” አሸተ ደምለው

135

ባሕርዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
የዞኑ ሕዝብ በአንድ በኩል ሰላሙን እያጸና ልማቱንም እየከወነ ነው። በቃብትያ ሁመራ ወረዳ ተጀምሮ ለዓመታት ቆሞ የነበረውን የቃብትያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታን በራስ አቅም ገንብቶ ማጠናቀቁ እና ማስመረቁም የዚሁ ማሳያ ነው።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው በሆስፒታል ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው በዞኑ ከደረሰው የዘር ጭፍጨፋ በተጨማሪ ከልማት ርቆ የነበረው ሕዝብ በራሱ መተዳደር ከጀመረ ወዲህ በርካታ መሠረተ ልማቶችን ገንብቷል ብለዋል።

በመሠረተ ልማቶቹ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት እና ተሳትፎ፤ የመሪዎችን አስቦ መሥራት በግልጽ እንደታየ ነው ያስረዱት። የዲያስፖራው ቁጭት በተግባር ተስተውሎበታል፤ ከወኔ የተነሱ ቅን ልቦች እና ለሥራ የሚተጉ ክንዶች ለምረቃ አብቅተውታል ነው ያሉት።

ጊዜው የትግል እና የሥራም ስለኾነ ሥራቸው ለዛሬው ብቻ ሳይኾን ለነገውም ትውልድ መሠረት ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተገነባው ሆስፒታል ትርክት ሥራን፤ ሥራም ትርክትን እንደሚቀይር አካባቢው አብነት ኾኗል ብለዋል።

የማይዝሉ ክንዶችን የትግል ውጤት ልንመርቅ ስንገናኝ ስለነዚያ ክንዶች ማንነት ማስታወስ ውቅያኖስን በጭልፋ ቢኾንም ማስታወሱ ተገቢ እንደኾነም ነው የተናገሩት። እነዚያ ብርቱ ክንዶች ሳይዝሉ ኖረዋል። እነዚያ ጀግኖች ከልባቸው እንደታጠቁ ዘመናትን ተሻግረዋል። የመከራውን ዳገት አልፈዋል። ለዕውነት ኖረው በዕውነት ታግለዋል። ስለ ዕውነት ጸንተዋል። የጨለማውን ዘመን በጽናት እና በጀግንነት አልፈዋል። የሰቆቃውን ማዕበል በብርታት ተሻግረዋል። ጣልናቸው ያላቸውን ጠላት በሰላማዊ እና ፍትሐዊ ትግል ጥለውታል። ቀበርናቸው ያሉትን ግፈኞች በታሪክ ፊት አስተምረዋቸዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊት ባላደራጀችበት ጊዜ ዳር ድንበር ጠባቂ ነበር ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነፍጥ አንጋች አርበኝነቱን በአምሥት ዓመቱ የጸረ ወረራ ተጋድሎ ማስመስከሩን አስታውሰዋል፡፡ “እኛ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አማራዎች ለፋሽስት ጣሊያን ያልተንበረከኩት የነደጃዝማች አዳነ መኮነን፣ የነፊታውራሪ ኃይሉ ፋሪስ፣ የነቀኛዝማች አባይ ወልደማርያም፣ የነቀኛዝማች መስፍን ረዳ፣ የነቀኛዝማች ገብሩ ገብረመስቀል ልጆች” ነን ሲሉም ዋኖቻቸውን ዘክረዋቸዋል፡፡ አርበኝነት ሥነ ልቦናዊ ውርስ ነውና የነሱ ልጆች ለአማራነታችን ኾነ ለኢትዮጵያዊ ማንነታችን ለነጻነት ክብራችን የማንከፍለው ዋጋ የለምም ብለዋል፡፡

ለፍትሐዊ ትግል የታመነ ማኅበረሰብ መገንባት የተቻለው መሪው እና ሕዝቡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመኾናችን ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነት ትህትና እና ጀግንነት ነውና የአባቶቻችን ትግል አስተዋይነት፣ አርቆ አሳቢነት እና ትዕግሥት ነው፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብም ተወልዶ ባደገበት ታሪክ እና ቃል ኪዳን በተቀበለበት ሥፍራ በልማት ላይ ይገኛል።

ለጤናማ ትውልድ ግንባታ ትልቅ መሠረት በሚጥለው የትምህርት እና ጤና መስክ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በአንድ በኩል ራሱን በራሱ ለማሥተዳደር የሚያበቃውን በሌላ በኩል ደግሞ የልማት ትግል እያደረገ የሚገኘው ሕዝብ በአማራ ልማት ማኅበር እና በሕዝቡ ተሳትፎ የዕውቀት በር የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ መቀመጥ እና የቃብትያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመጀመሪያ ዙር ግንባታ መጠናቀቅ ደስታው ልዩ ነው ብለዋል አቶ አሸተ፡፡

ከዓመታት የጸና ተጋድሎ እና መስዋዕትነት በኋላ ነጻነቱን እያጣጣመ ያለው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ዙሪያ ያለው ሰላም የትጋቱ ውጤት እንደኾነም አስረድተዋል። በፍትሐዊ የትግል መንገድ ታምኖ በመጓዝ በጽናት ነጻነት እና ልማቱን አስጠብቆ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ሕዝቡ ነጻነቱን፣ ሰላሙን እና ማንነቱን እያጣጣመ ነው ያሉት አቶ አሸተ መንግሥትም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ጥያቄ በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ዕውቅና በመስጠት እንዲያረጋግጥለት በትዕግሥት እየጠበቀ መኾኑን አብራርተዋል፡፡  

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የሚታገለው አመለካከትን እንጂ የሚታገለው ሕዝብ የለውም ነው ያሉት። በማንም ላይም ጥላቻ የለውም፤ በማንነቱ ግን አይደራደርም፤ የሕዝቡን የማንነት ጥያቄ መመለስ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት እና ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ጣራና ማገር ነውም ብለዋል፡፡

ዋና አሥተዳዳሪው ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ያለ ሕገመንግሥት በወረራ ለ30 ዓመታት የተያዘውን መሬት ሕዝቡ ከኀይል ውጭ ዛሬ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲሰጠው የሕገ መንግሥት አንቀጽ ጠቅሶ የሚጠይቀው ሕግ እና ሥርዓት አክባሪ ስለኾነ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ዕውነታ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚያውቁት ነው የተናገሩት።

”የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የዘመናት የማንነት ትግል አዲስ ምዕራፍ እና የታሪክ እጥፋት ላይ ይገኛል” ያሉት አቶ አሸተ ጥያቄው በዘላቂነት እንዲቋጭ እና አማራነቱ እንዲረጋገጥለት ጥረት እያደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ 

ልማት፣ ሰላም እና ደኅንነት ሳይነጣጠሉ እንዲቀጥሉ ለማድረግ በአስተውሎት እና አርቆ አሳቢነት እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ 

ለመላው የኢትዮጵያ እና የአማራ ሕዝብ ብሎም በውጭ ላሉ ዲያስፖራዎች ለሰላም በርን ክፍት ማድረግ ማንነትን ለድርድር አሳልፎ መስጠት እንዳልኾነ እንዲረዱም አሳስበዋል፡፡ ሰላምን የወደደ እና ሕግን የተከተለ ሰው ሁሌ አሸናፊ ነውም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስከፊውን የማሕጸን ጫፍ በር ካንሠር ለመከላከል ለልጃገረዶች ክትባት እየተሰጠ ነው።
Next articleሰላም እና ልማታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።