የሌማት ትሩፋት ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ መኾኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ገለጹ።

38

ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህና ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኘውን የደብረ ሆላንድ የዶሮ ርባታ ማዕከል ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ሚኒስትሮች፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በጉብኝቱ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) የሌማት ትሩፋት ትልቅ እምርታ እየተመዘገበበት መኾኑን ተናግረዋል። በዶሮ ርባታ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ መኾኑንም ገልጸዋል። ነገር ግን አሁንም በቂ አይደለም ነው ያሉት።

በዶሮ ርባታ ብቻ ሳይኾን በሌሎች የሌማት ትሩፋት ሥራዎችም ለውጥ እየመጣ መኾኑን ነው የገለጹት። እንደ ደብረ ሆላንድ አይነቶቹ የዶሮ ርባታ ማዕከላት የሌማት ትሩፋት እንዲያድግ፣ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር እና ለወጣቶች የሥራ እድል እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለው መኾኑንም ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት ውጤቱ በአጭር ጊዜ የሚታይ፣ አዋጭ የኾነ፣ በፍጥነት ሃብት የሚገኝበት መኾኑን ነው የገለጹት። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የእንስሳት አረባብ ዘዴ ባሕላዊ እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሩ አሁን ላይ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የመኖ ሥራውን በስፋት መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲገቡ እናበረታታለን ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ለሌማት ትሩፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገለጹ።
Next articleአስከፊውን የማሕጸን ጫፍ በር ካንሠር ለመከላከል ለልጃገረዶች ክትባት እየተሰጠ ነው።