
አዲስ አበባ: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፍ ዞን ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በኮረሪማ ቅመም መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል። የጎፋ ዞን በሀገሪቱ በቅመማ ቅመም ምርት አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። ደጋማ እና ተራራማ በኾኑ የጎፋ ዞን ወረዳዎች አርሶ አደሮች ማሳቸውን በቅመማ ቅምን በመሸፈን ተጠቃሚ መሆናቸውን የብሔረሰቦች በዓልን አስመልክቶ ጉብኝት ባደረግንበት ወቅት ነግረውናል።
አርሶ አደር ሁሴን ኡቴ በዞኑ በገዜ ጎፋ ወረዳ የድሮ ኤላ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። 30 ኩንታል ኮረሪማ በአንድ ሔክታር በማምረት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን አርሶ አደሩ ተናግረዋል።
በዞኑ በሚገኘው ዛላ የተባለ ወረዳም አሪቲ ቅምም ይመረታል። በወረዳዉ 6 ሺህ 270 ሄክታር ማሳ በአርቲ ቅመም መሸፈኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል። አርሶ አደር አዲሱ ዋኔ በዛላ ወረዳ ዳዳ ጋላይሲ ቀበሌ አሪቲ ያመርታሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እያደገ በመምጣቱና ኑሯቸው መሻሻሉን አስረድተዋል።
ቅመማ ቅመም የኢንዱስትሪ ምርቶች እየሆኑ በመምጣታቸው የአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል። በመምሪያው የቡና እና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ቡድን መሪው ኑርአዲስ አደም በዞኑ በኮረሪማ ብቻ 15 ሺህ 316 ሄክታር ማሳ እየለማ ነው ብለዋል። አርቲ፣ ኮረሪማ እና ሮዝመሪ አየለሙ ነው፤ የአርሶ አደሮችን የገበያ ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዞኑ ዝንጅብል፣ ሮዝመሪ፣ አርቲ እና ኮረሪማን ጨምሮ በጥቅሉ 30 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም ተሸፍኗል ።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!