
ባሕርዳር: ኅዳር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተያዘው የምርት ዘመን በአማራ ክልል የሰብል አያያዙ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ተብሏል። ከፍተኛ የምርት አቅም ያለው ክልሉ ምርት እና ምርታማነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እየተጠበቀ መኾኑን ገልጸዋል።
“በክልሉ ያለው የሠብል ግምገማ ያቀድነውን ዕቅድ ያለምንም ችግር ማሳካት እንደምንችል የሚያሳይ ነው” ብለዋል። በመስክ ግምገማችን የግብዓት አቅርቦት ሥራችን መሬት ላይ ምን ያክል ውጤት እያመጣ እንደኾነ አይተናል ነው ያሉት። ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ማሰራጨታቸውንም አስታውሰዋል። ከ180 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን መጠቀማቸውንም ገልጸዋል። ሰብልን በኩታ ገጠም ማምረት እና ምክረ ሃሳብን መተግበር የተሻለ ለውጥ እንደታየበትም ተናግረዋል።
በክልሉ ሠብል እየተሠበሠበ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ገና በማሸት እና በመድረቅ ላይ ያለ ሠብል መኖሩንም አስታውቀዋል። ዓመቱ የምርት ዓመት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ነው ያሉት። ለግብርና ልማት ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ኀላፊው በሰላም ችግር ውስጥ ኾነውም ጥሩ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በመስኖ ልማት እና ለቀጣይ የመኸር ምርት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ሰላም ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል። በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ነው ያሉት። ክልሉን እየጎዳው ያለው አሁን ላይ እየመጣ ያለው የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ነው ያሉት ኀላፊው በሃሳብ ሞግቶ፣ ጥያቄን በጠረጴዛ ዙሪያ አቅርቦ መፍታት እየተቻለ ጸረ ዲሞክራሲ የኾነ አስተሳሰብ እየጎለበተ መምጣቱ እና አንዳንድ ጽንፈኛ ኀይሎች በአልተገባ መንገድ ፖለቲካውን በማዛባት ኅብረተሰቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዳይገባ አድርገውታል ብለዋል።
ሥርዓት አልበኝነትን እና ለአማራ ሕዝብ ባሕልና ታሪክ የማይመጥን አካሄድን ማኅበረሰቡ አምርሮ መታገል እንደሚገባውም ነው የተናገሩት። ከመንግሥት ጋር በመኾን ሰላምን ማረጋገጥ እና ድህነትን መዋጋት ይገባል ነው ያሉት። ሰላምን ማስከበር ቀዳሚው ተግባር መኾን እንደሚገባውም ነው ያመላከቱት።
መላ ኅብረተሰቡ ጊዜውን በማልማት ነው ማሳለፍ ያለበት ያሉት ኀላፊው በግጭት የለማ ሀገር የለም፣ ሁሉም ሰው ፊቱን ወደ ልማት አዙሮ ድህነትን መፋለም ይኖርበታል ብለዋል። እየተመረተ ያለው ምርት ተስፋ ሰጭ መኾኑንም ተናግረዋል።
የድኅረ ምርት ብክነት እንዳይኖር ሜካናይዜሽንን መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት። አርሶ አደሮች ገንዘብ ቆጥበው ኮምባይነር እየጠየቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ለማሟላት እየተሠራም ነው ብለዋል።
አርሶ አደሮች ሠብላቸውን በፍጥነት በመሠብሠብ የምርት ብክነትን እንዲቀንሱም አሳስበዋል። ምርትን ከገበያ ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ተጠቃሚ መኾን ይጠይቃል ነው ያሉት። አርሶ አደሮች ምርታቸውን በአግባቡ እንዲሠበሥቡም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!