የኮሮና ወረርሽኝ ብዙ ሠራተኞችን እስከወዲያኛው ከሥራ እንዳያሰናብት ተሰግቷል፡፡

112
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ወረርሽኝ አካላዊ ቅርርብን የማይፈቅድ በመሆኑ በዓለማቀፍ ደረጃ በርካታ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን በጊዜያዊነት እንዲያሳርፉ፣ አንዳንዶቹም ከሥራ እስከ ማሰናበት እንዲችሉ መብት እያገኙ ነው፡፡ በአሜሪካ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እንደተፈናቀሉ የሲ ኤን ቢ ሲ ዘገባ ያሳያል፤ ከእነዚህ የበለጡት ደግሞ ለጊዜው ዕረፍት ተሰጥቷቸዋል፤ ወረርሽኙ በአጭር ጊዜ ካልተገታም የመሠናበት ዕጣ ፋንታቸው አይቀሬ ነው፡፡
 
ቢቢሲ በዘላቂነት እነዚህ ሰዎች ሥራቸውን እንዳያጡ ስጋት የሚያጭር ዘገባ ይዞ ወጥቷል፤ ‘‘የኮሮና ወረርሽኝ ሰዎች ሥራቸውን በሮቦቶች እንዲነጠቁ ያደርግ ይሆን?’’ ሲል በሚጠይቅ ሰፊ ሀተታው፡፡ እርግጥ ሮቦቶች ሰው ሠራሽ ሰዎች ሆነው የሰዎችን የሥራ ዕድል በመንጠቅ ስጋት ከሆኑ ሰነባብተዋል፤ የኮሮና ወረርሽኝ ደግሞ የበለጠ ኩባንያዎች ከሰዎች ይልቅ ሮቦቶችን እንዲመርጡ የሚያስገድድ ሁኔታ ማምጣቱ የበለጠ ሰዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡
 
ቀድሞውንም በፋብሪካዎች ውስጥ በልዩ ልዩ የማምረት ተግባራት ሰዎችን ሲፎካሩ የነበሩት ሮቦቶች በኮሮና ምክንያት አብዛኛውን ሥራ የመቆጣጠር ዕድላቸው ሰፍቷል፡፡ ሰዎች የዓመት ዕረፍት ይጠይቃሉ፤ ሮቦቶች አይጠይቁም፡፡ ሰዎች ለቀን ስምንት ሰዓት በመደበኛ ደመወዝ ሠርተው ለተጨማሪ ሰዓት ተጨማሪ ክፍያ ይጠይቃሉ፤ ሮቦቶች ያለዕረፍትና ክፍያ ይሠራሉ፤ ሰዎች በወሬና ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ምክንያቶች ከሥራ ይዘናጋሉ፤ ምርታማነታቸው ወጥ አይሆንም፤ ሮቦቶች ወጥና ተመሳሳይ መጠን ያለው ሥራ በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ሮቦቶችን በቀጣሪዎች ዘንድ ተመራጭ ሲያደርጓቸው ሰዎች ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ የኩባንያ መሪዎችም ሰዎች ናቸውና ከሮቦቶች ይልቅ ለሰዎች እያደሉ ሰዎችን መቅጠርን ምርጫ አድርገው ቀጥለዋል፡፡
 
የዛሬው የትንሳኤ በዓል መሠረት የሆነው የክርስትና ሃይማኖት መመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰው ማኅበራዊነት ሲናገር ‘‘ሰው ብቻውን ይኾን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ረዳትን እንፍጠርለት’’ ብሎ በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ቁጥር 18 ቢያስተምርም ዛሬ ሰው ብቻውን እንዲሆን ጊዜ አስገድዷል፡፡ አሁን ዓለምን የገጠማት የኮሮና ወረርሽኝ ሰው ሰውን እንዲሸሽ፣ ሰው ብቻውን እንዲሆን አድርጓልና፡፡
 
ወረርሽኙ ኩባንያዎችን ከማምረት ስለገደባቸው ማሽኑን በማሽን ለማንቀሳቀስ ፊታቸውን ወደ ሮቦቶች እያዞሩ ነው፡፡ ሰጥ ለበጥ ብለው በምግብና መጠጥ ቤቶች የሚያስተናግዱ፤ ግን ጉርሻ (ቲፕ) የማይቀበሉ፣ በፋብሪካዎች ውስጥ ማሽኖችን የሚዘውሩ፣ የሕክምና ሥራዎችን ጭምር የሚያቀላጥፉ ሮቦቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ ታዲያ በወረርሽኙ ምክንያት ሰው ከሥራ ቦታ እንዲቀንሱ የተደረጉ ኩባንያዎች የቀነሷቸውን ሰዎች በሮቦት በመተካት እየተጠመዱ ነው፡፡
 
ቢቢሲ እንዳስነበበው ማርቲን ፎርድ የተባሉ ሰው ‘‘ሰዎች ሰዎችን ማሠራት ቢፈልጉም ኮሮና ሁኔታውን ቀይሮታል’’ ብለዋል፤ ይህም ለአስርት ዓመታት አዝጋሚ ዕድገት ያሳየውን ሰዎችን በሮቦት ተክቶ የማሠራት ሂደት በእጅጉ እንደሚያፈጥነው አስታውቀዋል፡፡
 
ሰዎችም በሰዎች ከመስተናገድ ይልቅ በሮቦቶች መስተናገድን እየመረጡ መሆኑን በማመላከትም ‘‘አጋጣሚው ለሮቦትና አውቶሜሽን (ያለሰው ለሚሰሩ ማሽኖች) ትንሳኤ ነው’’ ብለውታል፡፡
 
በተለይም ሰዎች ከቤታቸው ሆነው ማከናወን የማይችሏቸውን ሥራዎች ሮቦቶች ተክተው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑ በዘርፉ አዲስ አብዮት እንደሚያስከትል እየተገለጸ ነው፡፡ ለአብነት በአሜሪካ ግዙፉ የንግድ ተቋም ‘ዋልማርት’ የንግድ ማዕከላቱን ለማጽዳት ሮቦቶችን እየተጠቀመ ነው፤ ‘‘ሮቦቶቹን ውጤታማነታቸውን ሲያይ በኋላ የጽዳት ሠራተኛ ሰዎቹን ወደ ሥራ ይመልሳል ወይ?’ ያልተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡
 
በደቡብ ኮሪያ ሮቦቶች ከኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ ጋር በተያያዘ የሰዎችን ሙቀት በኢንፍራሬድ ቴርሞ ሜትር እየለኩ ነው፤ የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘርም እያደሉ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት እስከ ቀጣዩ የአውሮፓውያኑ ዓመት ድረስ አካላዊ መራራቅ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ የሮቦቶችን ተፈላጊነት ከፍ ማድረጉ ይጠበቃል፡፡
 
የንጽሕና መስጫና ሳኒታይዘር አምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ ምርት እንዲያቀርቡ እየተጠየቀ ነው፤ በዚያው ልክ ግን ምርቶቹን የሚያመርቱ ሠራተኞችን በየሥራ ክፍሎቹ መቀነስ ግዴታቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ኩባንያዎቹ የገበያውን ፍላጎት ለማርካት ሮቦቶችን እያሠማሩ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ የዴኒማርኩ በጨረር ተኅዋስያንን የሚያጠፉ ሮቦቶችን አምራች ኩባንያ በርካታ ሮቦቶችን አምርቶ ወደ መላው አውሮፓና ቻይና ማድረሱ ተሰምቷል፡፡ የምግብና መጠጥ ቤቶችም እነዚህ ሮቦቶች በአስተናጋጅነት እንዲሠሩላቸው እያደረጉ በመሆኑ ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡
 
አሁን አብዛኛው ዓለም የንግድ እንቅስቃሴው ስለተገታ እንጅ ወደ ሙሉ እንቅስቃሴው ቢመለስ በትምህርት ቤቶችና ቢሮዎችም ጠረጴዛ የሚጸዱ ሮቦቶች በብዛት ሲርመሰመሱ ማዬት አይቀሬ እንደሆነ ነው የቢቢሲ ዘገባ የሚያመላክተው፡፡
 
‘‘የወደፊት ደንበኞች’’ የሚል ትርጉም የያዘው (ዘ ከስተመር ኦፍ ዘ ፊውቸር) መጽሐፍ ደራሲ ብላክ ሞርጋን ‘‘ደንበኞች አሁን ከምንም በላይ ስለደኅንነታቸውና ስለሚያስተናግዷቸው ሰዎች ደኅንነትና ጤንነት ይጨነቃሉ፡፡ ወደ ሮቦት አገልግሎት መግባት ደግሞ ደንበኞችን የበለጠ ምቾት ይሰጣል፤ ጤንነታቸውም ይጠበቃል፤ ይህንን የሚያደርጉ ደግሞ ደንበኞቻቸው ይበዙላቸዋል’’ ብለዋል፡፡
 
በእርግጥ ብዙ የመረጃ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት አሁንም ደንበኞች በሰዎች ለመስተናገድ እንዲገደዱ እንደሚያደርግም ሞርጋን ተናግረዋል፡፡
ከጤና ጋር በተያያዘ ምግብ አቅራቢዎችና አብሳዮችም ሮቦቶች መሆናቸው እንደማይቀር እየተገለጸ ነው፡፡ የትኩስ ምግብ አቅራቢው ማክዶናልድ ምግብ አብሳይና አስተናጋጅ ሮቦቶችን እየሞከረ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
 
እንደ አማዞን እና ዋልማርት ያሉ ግዙፍ የገበያ ማዕከላትም ፍጥነትንና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ጭምር ሮቦቶችን እየተጠቀሙ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ደግሞ የበለጠ ምርቶችን በመለዬት፣ በማሸግና ማጓጓዝ ሮቦቶችን እንዲጠቀሙ ጫና እያሳደረባቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኩባንያዎቹ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ መቸገራቸውን ሲገልጹ የቆዩ ሠራተኞችን እህል ውኃ የሚበጥስ መፍትሔ ነው፡፡
 
ሮቦቶች አንዴ ከገዟቸው በኋላ ወጭ የማይጠይቁ መሆናቸው ለሠራተኞቹ እንደወጡ መቅረት ምክንያት ያደርጋቸዋል፡፡ መጀመሪያ ለመግዛትና ከትዕዛዛቱ ጋር ለማቀናጀት ከሚጠይቁት ወጪ በቀር ምንም የማያስወጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆናቸው ሮቦቶችን ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
 
ባንኮች በጥቂት ሰዎች እንዲሠሩ ያደረጉ የአውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ናቸው፤ ፀሐፊዎች እንዲመናመኑ ያደረጉ ላፕቶፖችና ስማርት ስልኮች ናቸው፤ የፖስታ ቤቶችን የደብዳቤ ሳጥኖች ያደረቁ ማኅበራዊ ሜዲያዎች ናቸው፡፡ በአውሮፓና አሜሪካ በሬ ለእርድ እንጅ ለእርሻ መዋል ከቀረ ሰነባብቷል፤ በሂደት የአፍሪካ በሬዎችም ከቀንበር እየወጡ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጀርባ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ሮቦቶችን አምርተው ሰውን ቦዘኔ እንዳያደርጉት ተሰግቷል፡፡
 
በተለይ ጉልበታቸውን ሸጠው የሚያድሩ የመኖሪያ ቤት ሠራተኞች፣ የጽዳት ሠራተኞች፣ የጉልበት ሠራተኞች፣ በሆቴሎችና ምግብና መጠጥ ቤቶች የሚሠሩ አስተናጋጆች እንጀራቸው እንዳይነጥፍ ስጋት ሆኗል፤ የሮቦት ቴክኖሎጂ፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ወደ ዐረብ ሀገራት፣ አውሮፓና አሜሪካ ጉልበታቸውን ሸጠው ለማደር የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንም እንጀራ በሮቦቶች መበላቱ ነው፡፡
 
በአብርሃም በዕውቀት
Previous articleየገንዳ-ውኃ ወጣት ማኅበራት ከኅብረተሰቡ በሰበሰቡት 86 ሺህ ብር በዓልን ለማክበር ለተቸገሩ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረጉ።
Next articleበኮሮና ‘ተሸልሜያለሁ’ የሚባለው እሳቤ አለመሥራቱን መረጃዎች እያረጋገጡ ነው፡፡