
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን የዓለም ሕዝብ የአሜሪካን ሀገራዊ ምርጫ ሲከታተል ሰንብቷል። የኀያላን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በሌሎች ሀገራት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ‘’ተፅዕኖ’’ የማሳደር አቅም ላቅ ያለ ስለኾነ ነው ዓለም ሁሉ የአሜሪካን ምርጫ በንቃት የሚከታተለው።
የምርጫውን ሂደት ከተከታተሉ ሰዎቸ አንዱ እኔ ነበርኩ። የዚህች ሀገር ብዙ ነገሯ መንፈሳዊ ቅናት ያሳድራል። ከሁሉም በበለጠ ግን ለሀሳብ ነጻነት የሰጡት ዕውቅና እጅጉን ያስደምመኛል። አሜሪካ ማንኛውም ግለሰብ የሚያምንበትም ኾነ አምኖበት የሚያንጸባርቀው ሀሳብ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይከበራል። ፍጹም ነው ማለት ግን አይደለም፤ በአንጻራዊነት እንጂ። ምክንያቱም ሰብዓዊ ነጻነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲኾን እየተደረገ ያለው የሰው ልጅ የትግል ጉዞው በሂደት ላይ ያለ እንጂ የተቋጨ የቤት ሥራ አይደለምና ነው።
ዛሬ የደረሱበት ላይ ለመድረስ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ሌሎች የነጻነት ታጋዮች የሕይዎት ዋጋ ከፍለዋል። አሜሪካዊያን ሁሉም ጉዳዮቻቸው በሀሳብ ጥላ ስር የሚያርፍ ነው። ከሀሳብ ልዩነት ተሻግሮ ወደ ግጭት ለሚሻገር ሁኔታ ቦታም ዕድልም አይሰጡም። በሀሳብ እስከፈለጉት ድረስ ሲነታረኩ እንመለከታለን።ይህ የሀሳብ ልዩነት ግን እህትማማችነትን፣ ወንድማማችነትን፣ መዋደድን፣ መከባበርን ሲያሳጣቸው አናስተውልም ።
የሥልጣን ርክክባቸውም ያላንዳች ኮሽታ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማከወናቸው ሌላኛው ”ምናለ ሀገሬም እንዲህ በኾነችልኝ” የሚያስብል ነው። ሰሞኑንም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ተሸናፊዋ ካማላ ሃሪስ እንደተሸነፈች ባወቀች ቅጽበት ለዶናልድ ትራምፕ ደውላ እንኳን ደስ አለህ ማለቷን ስትነግረን ይህ ልምምድ ለሌለን ለእንደኛ አይነቷ ሀገር አያስቀናም ትላላችሁ?
የሀሳብ ነጻነትን ያከብራሉ ስንል ለግለሰብ ሀሳብ ክብር አላቸው ማለቴ ነው።ጉዳያቸው ሁሉ ግለሰብን ከማክበር ይጀምራል። ምክንያቱም ማኅበረሰብ የግለሰቦች ሥብሥብ እንጂ ሌላ አይደለም። ግለሰብ እንደፈለገው እንዲያስብ፤ በተስማማው የሕይዎት ፍልስፍና እንዲመራ፤ የወደደውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲደግፍ ነጻነቱ ተሰጥቶታል። ለምን ይህንን ተናገርክ ለምን እገሌ የተባለውን ፓርቲ ደገፍክ ብሎ የሚያስፈራራው የለም። አንድ ግለሰብ “እገሌ የተባለውን ፓርቲ በመደገፌ ማስፈራሪያ ደረሰብኝ” ብሎ ቢናገር በሁሉም የሀገሪቱ ሚዲያዎች አስደንጋጭ ሰበር ዜና ይሆናል።
ሌላው የአሜሪካዊያን የሚያስገርመው ሥልጣኔአቸው አንድን ነገር ሲደግፉም ኾነ ሲቃወሙ ምክንያታዊ ኾነው ነው። በበለው በለው እና በያዘው ያዘው የሚነዳ ስሜት የላቸውም። ትራምፕንም ኾነ ካማላ ሃሪስን ሲደግፉም ኾነ ሲቃወሙ ለታላቋ አሜሪካ እና አሜሪካዊያን ካላቸው ዕቅድ ተነስተው እንጂ የተወለዱበትን ጎሳ ወይም ባላቸው የቆዳ ቀለም አይደለም።
ሰሞኑን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኀን የሚያወጧቸውን ዘገባዎች ስመለከት በዶናልድ ትራምፕ እና በካማላ ሃሪስ እንዲሁም እነዚህን ተፎካካሪዎች በሚደግፉት አሜሪካዊያን ያለው ልዩነት እጅግ የጎላ ነው። ይህ ግን ከሀሳብ ልዩነት ተሻግሮ ጦር ወደ መማዘዝም ኾነ ወደ ሌላ ፍልሚያ አይወስዱትም። ደጋፊዎቻቸውም በድንጋይ አይፈናከቱም። በቡጢ አይናረቱም።ሁሉም ጉዳያቸው መዳረሻው በሀሳብ ብቻ ነው። አሸናፊው ሀሳብ ብቻ ነው።
እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንምጣ። እኛ ሀገር የግለሰብ ሀሳብ ፍጹማዊ ሳይኾን የመንጋው ሀሳብ የበላይነት አለው። የሚከበረው መንጋውን ያስገኘው “ግለሰቡ” ሳይኾን የግለሰቦች ሥብሥብ የኾነው መንጋው ሕያው ይኾናል። በአንድ ሥብሥብ ውስጥ ያሉ ሁሉም ግለሰቦች ግን በሀሳባቸው ተመሳሳይ ኾነው አይደለም፤ ሀሳባቸው እየተጨፈለቀ እንጂ። ሀሳባቸው በብዙኀኑ ተውጦ ብቻ ቢቀር ግን ምንኛ በታደልን ነበር።
የተለየ ሀሳብ ያለው ሰው ውግዘት ይደርስበታል። ማሸማቀቅ ይፈጸምበታል። እኛ ሀገር እኔ ትክክል ነኝ ስንል ሌላውም ለራሱ ትክክል ነው ብሎ ለማሰብ ፈጽሞ ዝግጁ አይደለንም። የኾነ የዕምነት ተቋም አባል እንደኾን ሁሉ ሌላውም ይህ መብት እንዳለው፤ የኾነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የመደገፍ መብት እንደተጎናጸፍን ሌላውም የፈለገውን መደገፍ እንደሚችል ከማንም ፈቃድ እና ዕውቅና የሚሰጠው ሳይኾን በሰውነቱ የተሰጠው ጸጋ መኾኑን ለማመን አምኖም ለመቀበል አንፈልግም።
የሀሳብ ልዩነቶቻችን ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ሲያስቀሩብን ይስተዋላል። በርካታ ጓደኝነት በሀሳብ ልዩነት ብቻ ወደ ግጭት አምርቷል። ስንት ጉርብትናስ በሀሳብ ልዩነት ብቻ በጥላቻ ተደምድሟል። ስንት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳብ ልዩነቶቻቸው ብቻ ኢትዮጵያን የጦርነት መዓት አምጥተውባታል?
ጸሐፊ ቢልልኝ ሀብታሙ “ሰው መኾን” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፉ “ልዩነታችን ጤነኝነት ሳይኾን በሽታ ተደርጎ ይቆጠራል። ልዩነትህን ሊያስተናግድህ ስላልቻለ ብቻ እንደ ወንጀለኛም ይቆጥርሃል” ይላል። ዋነኛው የሀገራችን ችግር ምንጩ ይህ ይመስለኛል። የሀሳብን ልዩነት እንደ ተፈጥሮአዊ ጸጋ የምንረዳ ብንኾን ኖሮማ በርካታ ጉዳዮቻችን በሀሳብ ብቻ ይደመደሙ ነበር እንጂ ለአፈሙዝ ፍልሚያ አይዳርጉንም ነበር።
ሁላችንም አሸናፊ የሚያደርገንን ሳይኾን አንዱ ጠፍቶ ሌላኛው ብቻውን ነግሶ የሚቀመጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንታትራለን። ስንት ጦርነቶችን አስተናገድን? ስንት በርካታ ውድመት ያስከተሉ ተቃውሞዎችን አደረግን? እነዚህ ሁሉ መጀመሪያ ሀሳብ የነበሩ እንደ ሀሳብነት ብቻ ሳንቆጥራቸው ወደ ፍልሚያ የወሰድናቸው ናቸው። በሀሳብ ልንለያይ እንችላለን እስከ ልዩነታችን ግን ሁላችንም የመኖር መብት አለን ብለን የምናምን ስንቶቻችን ነን?
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳና በረከት” በሚለው መጽሐፋቸው ታሪኮቻችንን ትጥቅ ማስፈታት አለብን ይላሉ። ዕውነት ነው። እኔ ግን እላለሁ ሀሳቦቻችንንም ትጥቅ ማስፈታት አለብን።
የምናንጸባርቃቸው ሀሳቦች ከጀርባቸው ስውር አፈሙዝ የታጠቁ ናቸው። ከተሸነፍኩ አፈሙዝ አነሳለሁ ብለን የያዝናቸው ናቸው። የሀሳብ ልዩነትን የማናከብር መኾናችንን የሚያሳይ ሌላ ማሳያም ላንሳ። ዶክተር መክብብ ጣሰው የስሜት ልህቀት በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለተለያዩ ጉዳዮች ሥብሠባ ሲኖራቸው የዚያ ግዛት ፖሊስ ዲፓርትመንት ኢትዮጵያዊያኑ በተሠበሠቡበት አካባቢ ለጥበቃ በርከት ያለ ኀይል እንደሚመደብ ይህም የኾነበት ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ሲሠባሠቡ ብዙ ግዜ በሀሳቦቻቸው ልዩነት የተነሳ ይደባደባሉ ከሚል እሳቤ መኾኑን የአንድ ግዛት ፖሊስ ሙያ ላይ የተሰማራ አሜሪካዊ እንደነገራቸው ጽፈዋል።
በሰው ሀገር በስደት እየኖርን እንኳን አመላችንን በጉያችን መያዝ አልቻልንም ማለት ነው። ስሜታዊነት ይነዳናል ማለት ነው፡፡ ልዩነት ውበት ኾኖ ሳለ ታዲያ ውበት አልባ የኾነውን ነጠላነት ለምን እንመርጣለን? የቀስተደመናን ውበት በርካቶች የሚደመሙት በርካታ የተለያዩ አይነት ቀለማትን ሠብሥቦ ስለያዘ ይመስለኛል፡፡ ልዩነትን እንደ ውበት እና ሰዋዊ ተፈጥሮ አድርገን አለመቀበላችን ብዙ ጉዳዮቻችን ወደ ግጭት እንዲያመሩ አድርጓቸዋል ብየ አስባለው፡፡
የሀሳቦቻችን መደምደሚያ አመጽ ማድረግ የከራረመብን ልማድ ነው። ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረውን የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ስናይ መጀመሪያ የሀሳብ ልዩነት የነበሩ ቀስ በቀስ ግን ሁሉም መደምደሚያቸው የኾነው አፈሙዝ ነው።
የበርካቶችን ሕይዎት ቀጥፏል። ለዚያውም “የቆምኩት ለአንተ መብት እና ነጻነት ነው” የተባለውን ሕዝብ ሕይዎት ነው የሚቀጥፉት ። በርካታ የታሪክ መጽሐፍትን ስናነብ የምንታዘበው ይህንን ነው። የተነሱት ጉዳዮች ግን በሀሳብ የሚፈቱ ነበሩ። ባይፈቱም እንኳን ወደ ጦርነት ገብተን በርካቶች ሕይዎታቸውን ከሚያጡ ሳይፈታም ቀርቶ ሰዎች እንዳይሞቱ ማድረግ የበለጠ አትራፊ ያደርገን ነበር።
በሀሳብ ልዩነትን መፍታት የሥልጡንነት መለያ ነው። አሜሪካዊያን ለሀሳብ ልዩነት ያላቸው ከበሬታ ያስቀናኛል ያልኩትም ይህን ድንቅ ሥልጣኔአቸው ስለሚደንቀኝ ነው፡፡
እናም በብዙ የሀሳብ ልዩነት ውስጥ አብሮ መኖርም ምልዑነት ነውና መዳረሻችን በሀሳብ ጥላ ስር ብቻ ቢሆን እላለሁ። ሰላም ለኢትዮጵያ
#ትዝብት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!