የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በተለየ መልኩ በየቤቱ እየተከበረ ነው፡፡

304

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል የምሥራቅ ኦሪዮንታል አብያተ ክርስቲያናትን በሚከተሉ ሀገራት ዛሬ እየተከበረ ነው፡፡ በዓሉን ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ሶሪያ፣ አውስትራሊያና ሌሎችም በድምቀት ያከብሩታል፡፡ ነገር ግን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ሀገራት ምዕመናን በየቤታቸው ሆነው ለብቻ በዓለ ትንሳኤውን እያከበሩ ነው፡፡

ዐረብ ኒውስ እንደዘገበው በግብጽ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያ ተክርስቲያናት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጥቂት የሃይማኖት አባቶች ብቻ ከውነዋል፡፡ የግብጽ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል ባስተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት ከምሽት 2፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 እንቅስቃሴ የተገደበ ነው፤ በማንኛውም ምክንያት ሃይማኖታዊም ይሁን ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ መሰባሰብም ፍጹም ክልክል ነው፡፡ አካላዊ ርቀትን መጠበቅም ግዴታ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የግብጽ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን በየቤታቸው ሆነው እያከበሩ እንደሆነ ዘገባው አስታውቋል፡፡

የአሌክሳንደሪያ ቅዱስ ማርቆስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቴዎድሮስ ሁለተኛ በመሩት የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጸሎት የሃይማኖት አባቶች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ታይተዋል፡፡ ለምዕመኑ አብነት መሆናቸውንም ዐረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ሥርዓቱም በአብዛኞቹ የግብጽ የቴሌቪዥን ጣብያዎች በቀጥታ ተላልፏል፡፡

የትንሳኤ በዓል በዩክሬንም በልዩ ልዩ ሥርዓቶች በድምቀት ይከበራል፡፡ ዩክሬናውያን የኦርቶዶክስና ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን ልክ እንደ ሌሎች የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት እያከበሩ ነው፡፡ በዓሉ በዩክሬን በከፍተኛ ማኅበራዊ መሰባሰብና ልዩ ልዩ ድምቀቶች የሚከበር ቢሆንም ዘንድሮ በዚህ መልኩ አልተከበረም፡፡ ምዕመናን በየቤታቸው ሆነው በጥንቃቄ ማክበርን መርጠዋል፡፡

በአውስትራሊያ የሚገኙ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችም የትንሳኤ በዓልን በቤታቸው በመሆን አክብረዋል፡፡ በአውስትራሊያ የትንሳኤ በዓል ሥነ ሥርዓት በቀጥታ በቴሌቪዥንና በማኅበራዊ ገጾች በስፋት እየተላለፈ ሰዎች በየቤታቸው ሆነው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ እያከበሩት ነው፡፡
ኤስ ቢ ኤስ ኒውስ በዘገባው ‘‘አውስትራሊያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የትንሳኤ በዓልን በቤታቸው ሆነው በማክበር የሌላውን ዓለም በቤት የመሆንና ራስን ከኮሮና የመጠበቅ ሁኔታ ተቀላቅለዋል’’ ብሏል፡፡

በአውስትራሊያ ሲድኒ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ረዳት ካኅን ፒተር ሞቭሮማቲስ ‘‘ለዓመታት ማኅበራዊ ሜዲያን ስንኮንን ነበር፤ አሁን በገጠመን ፈተና ግን መውጫ መንገድ ሆኖናል፤ ለምዕመናን ሥርዓቱን በማኅበራዊ ሚዲያ እያደረስን ነው፡፡ ከመጥፎም ነገር በጎውን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ አሁን በጣም መጥፎው ወረርሽኙ ነው፤ ራሳችንን መጠበቅ አለብን’’ ብለዋል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleኽምጠ ዊከ-መጋቢት-30-2012
Next articleየገንዳ-ውኃ ወጣት ማኅበራት ከኅብረተሰቡ በሰበሰቡት 86 ሺህ ብር በዓልን ለማክበር ለተቸገሩ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረጉ።