
ሰቆጣ: ኅዳር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክረምቱ ሲለፋበት የነበረውን ሠብል ለመሠብሠብ የሚረባረብበት ወቅት ነው።
አርሶ አደሮቹ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሠብላቸውን እንዳያበላሽባቸው በቡድን እና በአደረጃጀት መሠብሠብን አይነተኛ የመሠብሠቢያ ዘዴ አድርገው ይጠቀማሉ።
በዚህ ወቅትም የተለያዩ አደረጃጀቶች በመፍጠር ሰብላቸውን እየሠበሠቡ እንደሚገኙ በሰቆጣ ከተማ 01 ቀበሌ ማሳ ውስጥ ገብተው ያገኘናቸው አርሶ አደሮች ይገልጻሉ።
አርሶ አደር ማሞ ባሕሩ ሰብላቸውንም ወበራ በተባለ ባሕላዊ የአሠባሠብ ዘዴ ተጠቅመው እየሠበሠቡ እንደኾነ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ቀሪ ሠብሎችን በዚሁ መንገድ እየተጋገዙ እንደሚሠበሥቡ ይናገራሉ።
ሌላኛው አርሶ አደር ጋሻው መርሳ ከአሁን በፊት የገብስ እና የጤፍ ሠብላቸውን እንደሠበሠቡ ገልጸው በልማታዊ ሴፍትኔት ያለሙትን የስንዴ ክላስተር በአደረጃጀት እየሠበሠቡ መኾኑን ገልጸዋል። ቀሪው አርሶ አደርም በወበራ እና በመደራጀት ሊሠበሥብ እንደሚገባ መክረዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ118ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር የተሸፈነ ሲኾን ከ85ሺህ ሄክታር በላይ የሚኾነው ሠብል ተሠብሥቧል ያሉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ኀይሌ ሞገስ ናቸው።
የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ የመሠብሠብ ባሕሉ የተጠናከረ መኾኑን ያነሱት አቶ ኀይሌ ለበጋ መስኖ ለመዘጋጀት እንዲረዳ አርሶ አደሩ በተደራጀ መንገድ እንዲሠበሥብ እየተደረገ መኾኑን ይናገራሉ።
በቀጣይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል ሠብል ለብክነት እንዳይጋለጥ አርሶ አደሮች በጥራት እና በፍጥነት ሠብላቸውን እንዲሠበሥቡ አሳበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!