የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች እንግዶችን በፍቅር ተቀብለው ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል።

103

አዲስ አበባ: ኅዳር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል ወደ አርባ ምንጭ ከተማ የሚገቡ እንግዶችን በፍቅር ተቀብለው ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። ነዋሪዎች የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ከአብሮነት ባሻገር ከተማዋን እና ኢኮኖሚያቸውን የሚያነቃቃ መኾኑን ገልጸዋል።

በዓሉ በአርባምንጭ በመከበሩ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ዝግጅትን አስመልክቶ በወላይታ ሶዶ ከተማ ስንዘዋወር በጦና አደባባይ ፎቶ በማንሳት ሥራ ላይ ያገኘናቸው የከተማዋ ወጣቶች ተስፋዬ ባዛ እና እዮብ በለጠ በዓሉ ከአብሮነት ባሻገር የሥራ እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

ወይዘሮ አበበች ኤካ እና አቶ ዘላለም ጴጥሮስ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ከተማቸው ወላይታ ሶዶ ከፍተኛ መነቃቀት ያላት መኾኗን ተናግረዋል። ይህም ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይኾን ለእንግዶቿም በጉልህ የሚታይ ስለመኾኑ ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት ከመጣ በኋላ ደግሞ የበለጠ ውበት መላበሷን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ የከተማዋን ነዋሪዎች ኢኮኖሚ ለመደገፍ ዐቢይ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

እንግዶች በውቧ አርባምንጭ በሚዘጋጀው በዓል ለመታደም ሲጓዙ በአጋጣሚው ወላይታ ሶዶንም ያያሉ፤ ይህም ከተማዋን ለማስተዋወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል ነዋሪዎች። እንግዶች ወደ በዓሉ ቦታ ሲሄዱም በሁሉም የከተማዋ በሮች ተቀብለው ለማስተናገድ እና ለመሸኘት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በዓሉ በድምቀት እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ማርቆስ (መንቆረር) ከተማ መሥራች ደጃዝማች ተድላ ጓሉ!
Next articleከ85ሺህ ሄክታር በላይ ሠብል መሠብሠብ መቻሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።