የደብረ ማርቆስ (መንቆረር) ከተማ መሥራች ደጃዝማች ተድላ ጓሉ!

267

ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደጃዝማች ተድላ የራስ መርዕድ ኃይሉ ዮሴዴቅ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ ደጃዝማች ብሩ ጎሹ የጎጃም ገዢ ሆነው ‹‹የበላይ ነኝ ለሚል መስፍን አልገብርም›› ሲሉ አንድ መነኩሴ ‹‹አልጋህን የሚወርሰው ተድላ ጓሉ ነው›› ብለው ስለነገሯቸው ደጃዝማች ብሩ ደራስጌ ይማሩ የነበሩትን ተድላን እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡

መነኩሴውም ‹‹ብታስረውም ብትገርፈውም የፈጣሪ ትዕዛዝ አይቀርምና ፍታው›› ብለው ላኩባቸው፡፡ ደጃዝማች ብሩም የመነኩሴውን ምክር በመቀበል፣ ‹‹እኔ በምገዛበት ሀገር እንዳትቀመጥ›› ብለው ተድላን አባረሯቸው፡፡
ተድላም ወደ አምሐራ ሳይንት ሄደው ደጃዝማች ትኩ ዘንድ አገልጋይነት ገቡ፡፡ ደጃዝማች ትኩም የተድላ ከእርሳቸው ጋር መኾን ከደጃዝማች ብሩ ጋር ያጣላኛል ብለው ስላሰቡ እና ደጃዝማች ብሩም ለደጃዝማች ትኩ መልዕክት ስለላኩባቸው ደጃዝማች ትኩ ልጅ ተድላን አሰናበቷቸው፡፡

ልጅ ተድላም ከአምሐራ ሳይንት ወደ ደራ ሄዱ፡፡ ደራ ሄደውም ከነቦሪ ቱሪ ጋር ቢቀመጡም ደጃዝማች ብሩ የማስፈራሪያ መልዕክት ልከው ተድላ እንዲባረሩ አደረጉ፡፡

የኋላ ኋላ ወደ ጎጃም ተመለሱ፤ በዚህም ጊዜ የአካባቢው ሕዝብ ደጃዝማች ብሩን በመፍራት አናስገባም ብሎ ከለከለ፡፡ በዚህ መሐል የተድላ ዘመዶች ተደላን ፊታውራሪ ጸጋ የተባሉት ቤት ወስደው ደበቋቸው፡፡ ፊታውራሪ ጸጋም ‹‹የደጃዝማች ብሩን ጠላት ደብቀህ አኑረሃል›› ተብለው ተከሰሱና አንድ ሺህ አሞሌ ጨው እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸው ቅጣታቸውን ከፈሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ራስ ዓሊ በደጃዝማች ብሩ ላይ ጦርነት ስላወጁባቸው የተድላ ጉዳይ ቀዘቀዘ፡፡

ደጃዝማች ብሩ ከደጃዝማች ካሳ ኀይሉ (የኋላው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ) ጋር ተዋግተው መሸነፋቸውን ሲሰሙ ተድላ ለደጃዝማች ካሳ ኃይሉ አገልጋይነት ገቡ፡፡ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉም ተድላ የደጃዝማች ጓሉ መርዕድ መኾናቸውን ስላወቁ የጎጃም ጦር አዛዥ አድርገው ሾሟቸው፡፡

ብዙም ሳይቆዩ ደጃዝማች ተድላ ጓሉ በደጃዝማች ካሳ ላይ ሸፈቱ፡፡ መንቆረር (የዛሬዋ ደብረ ማርቆስ) ላይ ተቀመጡ እና ደጃዝማች ካሳ የሾሟቸውን ሰዎች እየሻሩ የራሳቸውን ሰዎች ሾሙ፡፡ ከዚያም በኋላ ደጃዝማች ተድላ ጓሉ ከየአካባቢው ባላባቶች ጋር ጦርነቶችን እያደረጉ አሸነፉ፡፡

ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከነገሱ በኋላም ደጃዝማች ተድላ ጓሉን ለመያዝ ቢሞክሩም እያመለጡ አስቸገሩ፡፡ በተለይ ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ የጅብላን ምሽግ ለመስበር ያደረጉት ያልተሳካ ሙከራ እንዲሁም ደጃዝማች ተድላ ጓሉ አጅባራ በተባለ ቦታ ከመያዝ ለጥቂት ሲያመልጡ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የደጃዝማች ተድላ ጓሉን ወታደሮች የጨረሱበት አጋጣሚዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጎጃም ገዢ የነበሩት እና የደብረ ማርቆስ (መንቆረር) ከተማ መስራች የሆኑት ደጃዝማች ተድላ ጓሉ መርዕድ
ለ12 ዓመታት ያህል ካሥተዳደሩ በኋላ ታመው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በዚህ ሳምንት ኅዳር 6 ቀን 1860 ዓ.ም ነበር፡፡

👉ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ

ዐፄ ቴዎድሮስ አንድ ቀን ከመኮንኖቻቸው ጋር ሲጫወቱ በድንገት በጨዋታው መሐል “በዓለም ላይ ካለው ነገር ሁሉ ሽታው እጅግ ደስ የሚል እና ልብ የሚመስጥ ምንድን ነው?“ ብለው ጠየቁ:: መኳንንቱ ሁሉ የሚያውቁትን የሽቶ ዘርና ሌላም ሁሉ ነገር ተናገሩ፡፡

አጼ ቴዎድሮስም ሁሉንም አላወቃችሁትም ካሉ በኋላ “የሕጻን ልጅ ጠረን ነው“ ብለው መልሰውላቸዋል፡፡ ይህ የታሪክ ትውስታ አጼ ቴዎድሮስ ለልጅ የነበራቸውን ፍቅር የሚያሳይ እና ልዑል ዓለማየሁን ከወለዱ በኋላ ከልዑሉ ጋር እየተጫወቱ የሚያሳልፏቸው ጊዜያት እንደነበሩ እና ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡

ጳውሎስ ኞኞ “አጼ ቴዎድሮስ“ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቴዎድሮስ ስድስት ልጆች እንደነበሯቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከስድስቱ ልጆቻቸው መካከል ልዑል ዓለማየሁ ከትግራዩ የመጨረሻው የዘመነ መሳፍንት ባላባት የደጃች ውቤ ልጅ እቴጌ ጥሩ ወርቅ ነው የተወለደው፡፡

ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሚያዝያ አምስት 1853 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ እንደተወለደ ታሪክ ያስረዳል። ሕጻኑ በተወለደ ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ እጅግ ተደስተው መድፍ እና ጠመንጃ ማስተኮሳቸውን፣ አምስት መቶ ያህል እስረኞችንም መፍታታቸውን ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል። ከልጃቸው ጋርም ሲጫወቱ መዋል ያስደስታቸው ነበር፤ በተበሳጩ ጊዜ ዓለማየሁን አቅፈው ሲስሙ ሁሉንም ነገር ይረሱ ነበርም ይላሉ።

አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ ከእንግሊዞች ጋር ጦርነት ገጥመው ራሳቸውን ባጠፉ ወቅት ዓለማየሁ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ነበር። ንጉሡ ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ ሕጻኑ እና እናቱ እቴጌ ጥሩ ወርቅ ከእንግሊዝ ወታደሮች ጋር ወደ እንግሊዝ ጉዞ ጀምረው የነበረ ቢኾንም እቴጌዋ አንጣሎ አጠገብ ሐይቅ ሀላጥ የተባለ ስፍራ ሲደርሱ በህመም ምክንያት ሕይዎታቸው አለፈ። ይህም ለትንሹ ልዑል ከአባቱ ህልፈት ጋር ተደምሮ ድርብ ሃዘን ፈጥሮበታል፡፡

እቴጌ ጥሩ ወርቅ ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ለእንግሊዛዊው ካፒቴን ስፒዲ “ልጄ አባት የለውም፤ እኔም እናቱ ልሞት ነው፡፡ በሚሄድበት ሀገር ዘመድ ስለሌለው አንተ ዘመድ ሁነው፡፡ አባት ስለሌለው አንተ አባት ሁነው፡፡ ይሄን ያልኩህን እንደምታደርግለት በእግዚአብሔር ማልልኝ” እንዳሉት እና ካፒቴን ስፒዲ በኋላ ላይ በጻፈው መጽሐፍ እቴጌዋ የጠየቁትን እፈጽማለሁ ብሎ እንደማለ ጳውሎስ ኞኞ ጠቅሰዋል፡፡

ልዑል ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ የተወሰደው ፌሬዝ በምትባል መርከብ ሰኔ አራት ቀን 1860 ዓ.ም ነበር።

ካፒቴን ስፒዲ ትዳር ሳይመሰርት የቆየ ስለነበር ለዓለማየሁ ጥሩ አሳዳጊ እና እናት የምትሆን ወይዘሮ ኮታም የተሰኘች ሴትን መርጦ አገባ:: ወይዘሮ ኮታም ከዓለማየሁ ጋር በፍጥነት ተወዳጀች፤ ጥሩ አሳዳጊም ሆነችው::

ሆኖም የልዑል ዓለማየሁ ቀጣዩ ዕጣ ፋንታ እንደተጠበቀው አልነበረም። ምክንያቱም ምንም እንኳ ስፒዲ ለልጁ በማሰብ ሚስት ለማጋባት ቢወስንም ሥራውን መሥራት ስለነበረበት በወቅቱ ወደ እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሕንድ የስምንት ዓመቱን ዓለማየሁን እና ሚስቱን ይዞ አቀና:: በሕንድ በኖሩበት ሁለት ዓመታት ውስጥ ዓለማየሁ በትምህርቱ መጎበዝ መጀመሩ እና አልፎ አልፎ ከመታመሙ ውጭ ጥሩ ሁኔታ ላይ መኾኑን ስፒዲ በመጀመሪያ ሪፖርቱ ጠቅሶ ነበር፡፡

ይሁንና የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለሥልጣናት “ህንድ ለልዑል ዓለማየሁ ትምህርት ተመራጭ አይደለችም፤ ወደ እንግሊዝ ይመለስ እና ጥሩ ትምህርት ይከታተል” የሚል ሀሳብ አቀረቡ:: ህጻኑ ከስፒዲ ጥገኝነት መውጣት እንዳለበት እና ራሱን መቻል እንደሚያስፈልገውም ጠቀሱ:: ሀሳቡ ከፍተኛ ክርክር አስነሳ::

ስፒዲ እና ሚስቱ ዓለማየሁን በህንድ አሳልፎ ላለመስጠት እጅግ ቢሟገቱም የእንግሊዝ መንግሥት ልዑሉ ከህንድ እንዲመለስ ወሰነ:: በዚህ ጊዜ ዓለማየሁ በስፒዲ አንገት ተጠምጥሞ “አባቴ አንተ ነህ፣ ያለ አንተ መኖር አልችልም:: እባክህ ከአንተ አትለየኝ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ አብሬህ ልሂድ፤ ያለዚያ እሞትብሀለሁ…“ብሎ መናገሩን ጳውሎስ ኞኞ ይተርካሉ::

ልዑል ዓለማየሁ ቄስ ብላንኬ ለሚባል ዘጠኝ ሴት ልጆች ላሉት ሰው ተሰጠ። በቤቱ ውስጥ ብዙ ልጆች ስላሉ ልዑል ዓለማየሁ ባይተዋር እና ብቸኛ እንዳይሆን ታስቦ ነበር ውሳኔው የተላለፈው:: የካፒቴን ስፒዲ ጥገኛ እንዳይሆን እና በትካዜ ተውጦ ጊዜውን እንዳያሳልፍ በሚልም በሳምንት 31 ሰዓት ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ተደርጎ ነበር:: ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ቤት ውስጥም እንደታሰበው ከባይተዋርነት እና ናፍቆት ሊወጣ አልቻለም:: ሰውነቱ ገርጥቶ መጎሳቆል ጀመረ። በኋላ ላይ የልጁ መክሳት እና መጎሳቆል ንግሥት ቪክቶሪያን ጭምር ያስደነገጠ ነበር::

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ከአያቱ/ ከጥሩ ወርቅ እናት/ የተጻፈ ደብዳቤ ወደ እንግሊዝ ይደርሳል። ደብዳቤው የተጻፈው በአማርኛ በመኾኑ ተርጉሞ የሚያቀርበው ሰው አስፈለገ:: በዚህም የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዎልድሜር የተባለውን ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ አጼ ቴዎድሮስ የሚወዱት እና የሚያከብሩት መልዕክተኛን ፈልጎ አገኘ። ዎልድሜር ደብዳቤውን ተርጉሞ በእንግሊዝኛ አቀረበ:: የደብዳቤውም ይዘት ልዑሉ ለምን ለአያቱ ደብዳቤ እንደማይጽፍ፣ ወደ ሃበሻ ምድር ከቤተሰቦቹ እና ከወገኖቹ ጋር መቀላቀል እንዳለበት እንዲሁም የሀበሻ ሕዝብም የልዑሉን ተመልሶ መምጣት በጉጉት እንደሚጠብቅ የሚጠቅስ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ስለደብዳቤው እና ስለተሰጠው ምላሽ የሚታወቅ ነገር እንደሌላ ጸሐፊያን ጠቅሰዋል::

ልዑል ዓለማየሁ በቄስ ጄክስ ብላክ ቤት እንዳልተመቸው ከታወቀ በኋላ በተለያዩ እንግሊዛዊያን ሰዎች ቤት እንዲኖር ተደርጓል:: ኾኖም ከሁሉም ጋር በነበረው ቆይታም ስላልተመቸው በመጨረሻ ስሪል ራምሶን ከተባለ ሰው ጋር እንዲቆይ ተደረገ:: ራምሶን ለዓለማየሁ የተመቸ ነበር:: ከራምሶን ጋር የቆየው ዓለማየሁ የራግቢ እና የእግር ኳስ ጨዋታ ዝንባሌ እንደነበረውና የትምህርት አቀባበሉም እጅግ ጥሩ እንደነበር ይነገራል።

በዚያው እንደቆየ በጥቅምት ወር ታመመ:: ኖርዝ ኮት የተባለ ሐኪም ስለ ዓለማየሁ ሕመም ለሚመለከታቸው በጻፈው ደብዳቤ “አደገኛ ሕመም መታመሙን እንድታውቁ ይሁን:: ምንም ጥረት ብናደርግ ሕመሙ እየጸናበት ሔደ ሕመሙ አደገኛ በመኾኑ እና በጣም ስለጠናበት አሁን ምግብ አይበላም፤ መድኃኒትም አይወስድም”ሲል ገልጿል::

ንግሥት ቪክቶሪያን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናት መታመሙን ሲሰሙ ተጨነቁ። ንግሥቷም ማጽናኛ ደብዳቤ ላኩለት።

ልዑሉ ከንግሥቲቷ ደብዳቤ እንደመጣለት ሲያውቅ ተደሰተ። ነገር ግን ከሕመሙ የተነሳ አንብቦ ሊጨርሰው አልቻለም። በቅርብ ደብዳቤውን ከሚያይበት ቦታ እንዲቀመጥለት ጠይቆ ተቀመጠለት። ብዙም ሳይቆይ በዚህ ሳምንት ሕዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም በተወለደ በ19 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈች:: በንግሥቷ ትዕዛዝም ዊንድሰር በሚገኘው የነገሥታት መቀበሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጸመ::

👉የዩኒስኮ አመሠራረት

የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በኋላ በዚህ ሳምንት ኅዳር 7 ቀን 1938 ዓ.ም በእንግሊዝ ለንደን ተመሠረተ።

ድርጅቱ በ1945 ነው የተቋቋመው። የጦርነቱ ተፋላሚዎች የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ ስምምነቶችን መፈራረማቸው በቂ አይደለም ብሎ የተነሳው ዩኔስኮ፥ መላው ዓለምን በሚያስተሳስሩና የጋራ መግባባት በሚፈጥሩ ቅርሶች ላይ ሢሠራ ቆይቷል።

በፈረንጆቹ 1972ም የዓለም ቅርስ ኮንቬንሽንን አውጥቶ የሰው ልጅ ድንቅ የጥበብ ውጤት የሆኑ፣ ድንበር ተሻጋሪ ሰው ሠራሽ ወይም ባሕላዊ ቅርሶች እና የተፈጥሮ ሃብቶችን በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ጀምሯል።ዩኔስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ቅርስ አድርጎ የመዘገበው በኢኳዶር የሚገኙትን የጋላፓኮስ ደሴቶችና ውብ መልካዓ ምድርን ነበር።

ድርጅቱ እስካሁንም በ168 ሀገራት የሚገኙ 1 ሺህ 199 ቅርሶችን የዓለም ቅርስ አድርጎ መዝግቧል። ጣሊያን፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በርካታ ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዎቹ ሀገራት ናቸው። ኢትዮጵያም ዘጠኝ ባህላዊ እና ሁለት ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በማስመዝገብ 30ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በእንጅባራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleየወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች እንግዶችን በፍቅር ተቀብለው ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል።