
ደሴ: ኅዳር 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (ኤፍ ኤስ አር ፒ) ጋር በጋራ በመኾን “ዘመናዊ የትስስር መድረኮችን በመፍጠር እና የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት የኑሮ ውድነትን እናርግብ” በሚል የተዘጋጀ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎችን ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የግብይት ማዕከላትን በማስፋት አምራቹ እና ሸማቹ ተገናኝቶ ግብይት እንዲፈጽም ማስቻል፤ ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት እንዲሁም ትስስሩን በቴክኖሎጂ መደገፍ የሚያስችሉ አሠራሮች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ በከተማዋ ደረጃውን የጠበቀ ከ5 ሺህ ካሬ በላይ ቦታ የሚያርፍ የገበያ ማዕከል እንደሚገነባ ተናግረዋል።
መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ የገበያ ማዕከሉ ይገነባል ያሉት አቶ ዮናስ ለዚህም ከክልሉ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዘውገ ንጉሴ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እና ምርትን መደበቅ እንዳይኖር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) አምራቹን በቀጥታ ከሸማቹ ለማገናኘት ጊዜያዊ እና ቋሚ የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ዩኒየኖች እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት 906 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ሠልሀዲን ሠይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!