
ገንዳውኃ: ኅዳር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰሜን ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
ሁሉም መሪዎች ከቃል ባለፈ ወደ ተግባር በመግባት ወደታች አውርዶ ቀበሌዎች ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ አስገንዝበዋል።
ይህን ሰብዓዊ ተቋም እንደ ዜጋ ማንኛውም መንግሥት ሠራተኛ ኾነ የማኅበረሰብ ክፍል የሚሠራውን መልካም ተግባር አውቆ እና ተረድቶ የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰሜን ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ አታለል ታረቀኝ እንዳሉት ማኅበረሰቡ እና መሪዎች ቀይ መስቀልን በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አታለል ታረቀኝ ተቋሙን ለመክፈት ቅድሚያ የመስሪያ ቦታ እንደሚያስፈልግ በመረዳት የመሥሪያ ቦታ እንዲሠጥም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን አቃቢ ሕግ መምሪያ ኀላፊ ቢተው አሳየ ለተለያዩ የሥራ ኀላፈዎች ግንዛቤ በመፍጠር እና በማሳተፍ ታች ድረስ ወርደው እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ግብር ለመክፈል በሚመጣበት ጊዜ ስለቀይ መስቀል በማስረዳት እና በማወያየት እገዛ እንዲያደርግ የሥራ ኀላፊዎች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ ቢተው ተናግረዋል።
የተበተኑ ደረሰኞችን በመሠብሠብ እና ለኅብረተሰቡ ስለቀይ መስቀል ዕውቅና በመፍጠር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ አብራርተዋል።
የመተማ ወረዳ አሥተዳዳሪ ደሳለኝ ሞገስ ለቀይ መስቀል ከራስ ባለፈ ሌሎች አባላትን ከማፍራት አኳያ ጠንክረው እንደሚሠሩ አሳውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!