በከሚሴ ከተማ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ሙሉ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ።

42

ከሚሴ: ኅዳር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ መምሪያ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ሙሉ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በከሚሴ ከተማ ተካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የመከላከያ መኮንኖች ተሳትፈዋል።

ሃሳባቸውን ለአሚኮ የሰጡ የከሚሴ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ እና የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለማውጣት ደብረ ብርሃን እና ደሴ ከተማ በመሄድ አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸዋል። አሁን ላይ በአካባቢያቸው አገልግሎቱ መጀመሩ ካልተፈለገ እንግልት እና ወጪ እንደሚያድናቸው ገልጸዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ መምሪያ ኀላፊ ሰይድ ሁሴን የተሽከርካሪ አሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንዲጀመር የሕዝቡ የረጅም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ መኾኑን ገልጸው አሁን ላይ መጀመሩ ለኅብረተሰቡ እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የተሽከርካሪ አሽከርካሪ ፈቃድ የረጅም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ችግር እንደ ነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ አገልግሎቱ መጀመሩ ችግር ፈች ስለመኾኑም ተናግረዋል። በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየውን ሕገ ወጥነት ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በቀጣይም የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በመለየት ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራ ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ እያከናዎነች ያለው የኮሪደር ልማት ሰው ተኮር ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት
Next articleየኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሥራን ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾናቸውን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ገለጹ።