
ባሕርዳር: ኅዳር 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሰው ተኮር በመኾኑ በጥናት የተደገፈ፣ በቂ ዝግጅት የተደረገበት እና በጥብቅ የኀላፊነት ስሜት ክትትል እየተደረገበት መኾኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
የኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአንዳንድ ወገኖች የኮሪደር ልማቱ በዘፈቀደ የሚከናዎን እንደኾነ እና ሰዎችም እየተፈናቀሉ ለሰብዓዊ ጥሰት እንደተዳረጉ ተደርጎ የሚናፈሰው የተሳሳተ እና የተዛባ መረጃ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ መንግሥት ሥራውን በጥናት እና በዕቅድ እየመራ እንደኾነም በመግለጫቸው ግልጽ አድርገዋል።
ለልማቱ ሲባልም ከቦታቸው ለሚነሱ ሰዎች ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እና ትክ ቦታ እንዲሁም የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታዎችም እንደሚሰጡ ነው ዶክተር ለገሰ የተናገሩት።
የልማት ሥራው በማኀበረሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድር ተደርጎም እየተሠራ መኾኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ዜጎችን ከነተቡ እና ለመኖር አስቸጋሪ ከኾኑ ቦታዎች በማውጣት ዘመናዊ እንዲሁም ውብ ወደ ኾኑ መንደሮች እንዲኖሩ እየተደረገ ስለመኾኑም ዶክተር ለገሰ አብራርተዋል።
አሁን ላይ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ ከተማን ከነበረችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ተሻለ የመኖሪያ ቦታነት ቀይሯታል ያሉት ሚኒስትሩ የክልል ከተሞችም ተሞክሮውን በመውሰድ እየሠሩበት ነው፤ የሚታይ ለውጥም ተገኝቷል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!