“ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ዛሬን አገልግሎ ለነገ የሚተርፍ ተቋም ገንብቶ ሊያልፍ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

46

አዲስ አበባ: ኅዳር 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰንዳፋ የተገነባውን የፎረንሲክ ምርመራ እና የልህቀት ማዕከልን መርቀው ለሥራ ክፍት አድርገዋል።

በየጊዜው የሚፈፀሙት ወንጀሎች በዓይነታቸው ውሥብሥብ እና ለምርመራ አቅምን የሚፈትኑ እየኾኑ በመምጣታቸው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ የታጠቀ የወንጀል ምርመራ ተቋም መገንባት የግድ ኾኗል።

በዓይነቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነ እና ለአፍሪካ ሀገራት የልህቀት እና የምርምር ማዕከል ኾኖ የሚያገለግል የዲጂታል ፎረንሲክ ማዕከል ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተገንብቶ ለሥራ ክፍት ኾኗል።

በመድረኩ የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል የተገነባው የፎረንሲክ የምርመራ እና የልህቀት ማዕከል ዘመኑን የዋጁ የፎረንሲክ የምርመራ ላብራቶሪዎች እና በወንጀል ምርመራ ክህሎታቸው የዳበረ ባለሙያዎችን የያዘ በመኾኑ ውሥብሥብ እና አስቸጋሪ የኾኑ ወንጀሎችን ለመመርመር ብሎም እልባት ለመስጠት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በክብር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በጥራት በመገንባት ለነገም እንዲሻገሩ የማድረግ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። ይህ በፌዴራል ፖሊስ የተገነባው የፎረንሲክ ምርመራ እና የልህቀት ማዕከል አንዱ ማሳያ ተግባር ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከዘመኑ ጋር እኩል የሚራመድ ሕግ አስከባሪ ተቋማትን መገንባት ካልተቻለ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቋቋም ያስቸግራል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገነባው ማዕከል ፌዴራል ፖሊስ ወደ ተፈለገው አቋም እየመጣ መኾኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የተሠራው ሥራ የሚበረታታ ቢኾንም ለማደግ የሚጓጓ ሀገር በትንንሽ ስኬቶች መርካት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በኮሪደር ልማቱ መጠቀም መጀሯን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን አገልግሎት አስታወቀ።
Next article“ኢትዮጵያ እያከናዎነች ያለው የኮሪደር ልማት ሰው ተኮር ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት