
ባሕር ዳር: ኅዳር 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሃብት ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉት የአፍሪካ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት እንደምትገኝ ጠቅሰዋል። የዕድገቷን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና የማደግ አቅሟን ለመክፈት የኮሪደር ልማትን እንደ ቁልፍ ስትራቴጂ እንደወሰደች ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ተጀምሯል ያሉት ዶክተር ለገሰ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተከናዎኑ ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ መቀየራቸውን ገልጸዋል። ልማቱ ለአዲስ አበባ ደማቅ የውበት ብርሃን አላብሷታል ነው ያሉት። ጥሩ ያልነበሩ የመዲናዋ ሰፈሮች በኮሪደር ልማት ለኑሮ ምቹ እና አጓጊ ኾነው መታደሳቸውንም ዶክተር ለገሰ አብራርተዋል።
ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሳለጥ፣ የዘመነ ከተማ እንዲከተም እንዲሁም የሃብት ፈጠራ እንዲጎለብት የኮሪደር ልማቱ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። አሁን ላይ 30 በሚኾኑ የክልል ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ የገጠር የኮሪደር ልማትም ሰው ተኮር በኾነ መንገድ ይተገበራል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!