
አዲስ አበባ: ኅዳር 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 12ኛው የፌዴሬሽኑ አባል ከኾነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መካከል አንዱ የኾነው የዲላ ከተማ 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ለማክበር መዘጋጀቱን ነዋሪዎች እና ከተማ አሥተዳደሩ ገልጸዋል፡፡
የዲላ ከተማ ነዋሪ አቶ ሞላ ቦልጆ ከተማቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያላት መነቃቃት የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡
የዲላ ከተማ መነቃቃት የክልል ማዕከል ከመኾኗ ጋር የሚያያዝ ነው ብለው እንደሚያስቡም ለአሚኮ አስረድተዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ ተሞክሮ በመውሰድ በከተማዋ የጀመረው የኮሪደር ልማት፤ አብሮነትን ለማጠናከር የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እና ሌሎች ኮንፈረንሶች ለሚመጡ እንግዶች ጥሩ ዕይታን የሚፈጥር እንደኾነም ገልጸዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አብሮ መኖርን የሚያጠናክር በመኾኑ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለማክበር ዝግጅት ማድረጋቸውን ነግረውናል።
የዲላ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ታሪኩ በየነ የዲላ ከተማ ያለባትን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እየፈታች ያለች ከተማ መኾኗን ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሁሉም ነዋሪ እና ብሔር ብሔረሰቦ የሚፈልጓት ከተማ ለማድረግም እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደ ክልል የብሔረሰቦች በዓል አዘጋጅ በመኾናቸው ደስተኞች እንደኾኑም ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡
አንደ ከተማ ብዝኀነትን እና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት ስለማድረጋቸም ለአሚኮ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን፡ ጌዲዮ ዲላ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!