
አዲስ አበባ: ኅዳር 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫም በአማራ ክልል ያለው የጽንፈኛ ኀይል በአማራ ክልል ትምህር እንዲቋረጥ እና ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ተገኝተው እንዳይማሩ አድርጓል ብለዋል።
ክልሉ የወባ እና የተለያዩ የወረርሽኝ በሽታዎች የሚያጠቃው ቢኾንም የጤና ባለሙያዎች አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ተደርጓል ነው ያሉት።
ጽንፈኛ ቡድኑ የጤና ባለሙያዎችን ከማገቱም በላይ መሠረተ ልማቶችን እያወደመ ይገኛልም ነው ያሉት።
ሚኒስትሩ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ሸኔም ዜጎች ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳይችሉ ከማድረጉ ባለፈ ዜጎች መሠረታዊ አገልግሎት የሚያገኙባቸውን ተቋማት እያወደመ ይገኛል ብለዋል።
መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በተጠናከረ ሁኔታ እያካሄደ መኾኑን በመግለጽ ማኅበረሰቡ ይህንን የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዲደግፍም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልሳ ግዑሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!