
ሰቆጣ: ኅዳር 7/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ቤተ አምሃራ የልማት እና በጎ አድራጎት ድርጅት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጻግቭጂ ወረዳ ለሚኖሩ እና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የወሎ ቤተ አምሃራ የልማት እና በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ ይርጋለም ታደሰ ድርጅቱ “ከኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ” ጋር በመተባበር ግምቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የኾነ ሰብዓዊ ድጋፍ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ሀረቡ፣ በሰሜን ወሎ መርሳ እና በዋግ ኽምራ ጻግቭጂ ወረዳ ለሚገኙ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ ለጻግቭጂ ወረዳ ግምቱ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የኾነ የፊኖ ዱቄት መደገፋቸውን ነው የተናገሩት።
ድርጅቱ ከአሁን በፊትም በድርቅ ለተጎዱ ለሰሃላ ሰየምት፣ ለዝቋላ እና ለጻግቭጂ ወረዳዎች ለሚገኙ ወገኖች የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ይርጋለም ጠቁመዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የጻግቭጂ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ንጉሱ ደሳለኝ ባለፈው ክረምት በነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት፣ በበረዶ እና በጎርፍ አደጋ ምክንያት የምርት መጠኑ በመቀነሱ እና ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ወደ ቀያቸው ያልተመለሱ ከ4 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ገልጸዋል።
በአካባቢው ያለው አንጻራዊ ሰላም የሚያበረታታ እንደኾነ ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው በወረዳው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የመንግሥትን ድጋፍ የሚፈልግ ነው ብለዋል።
የወሎ ቤተ አምሃራ በጎ አድራጎት ድርጅት ያደረገው ድጋፍ ለ400 ተጎጂ እናቶች እና ሕጻናት የወር ቀለብ እንደሚኾን የገለጹት አቶ ንጉሱ ስላደረጉት ድጋፍ በሕዝቡ ስም ምሥጋና አቅርበዋል።
ሰብዓዊ ድጋፉን ሲከፋፈሉ አሚኮ ያገኛቸው የጻግቭጂ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብርሃ ወንድም ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመሥግነው መንግሥት አካባቢው ሰላም እንዲኾን የጀመረውን የሰላም ጥረት በማስቀጠል ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል። ማሳዎቻችን ጾም እንዳያድሩ፣ አርሶ አደሩ ሠርቶ እንዲበላ ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል አቶ አብርሃ።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ መለሱ ንጉሱ የተደረገው ድጋፍ ወቅታዊ እና ለአጥቢ እናቶች አስፈላጊ መኾኑን አውስተው ድጋፉን ለአበረከተው ድርጅትም ምሥጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሠርተው ለመብላት እንደተዘጋጁ የገለጹት ወይዘሮ መለሱ መንግሥት ሰላምን በማስከበር ወደ ነበረው ሰላም እንዲመልሳቸው ነው የጠየቁት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!