የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ወንጀለኞችን በሕግ እንዲጠየቁ ማድረጉን አስታወቀ።

62

ባሕር ዳር: ኅዳር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የወንጀል ዐቃቢ ሕግ አዲሱ መንግሥት በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሠራተኛ የኾኑ እና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ ሠራተኞች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ መወሰኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ የኾኑት ተከሳሾች የባንኩን ደንበኛ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጎንደር ቅርንጫፍ የነበራቸውን 387 ሺህ ብር በሞባይል ባንኪንግ በማውጣት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው እንደነበር አንስተዋል። ባንኩም ለደንበኛው ብሩን ከነወለዱ የመለሰ በመኾኑ በባንኩ ላይ ጉዳት ደርሷል።

ተከሳሾችም በፈፀሙት በዋና ወንጀል እና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በ1996 ዓ.ም የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ፤33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2ዐዐ7 አንቀጽ13/2/ የተመለከተውን በመተላለፍ የባንኩን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ወንጀል የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ አዘጋጅቶ እና ማስረጃዎችን አሰባስቦ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡

በክስ ሂደቱ 1ኛ ተከሣሽ ባለመያዙ ለጊዜው ክሱ የተቋረጠ ሲኾን 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ድርጊቱ የተፈፀመ መኾኑን አምነው ነገር ግን የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም በማለት ፍርድ ቤት ቀርበው ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር በመስማት እና ከክሱ ጋር ተያይዘው የቀረቡትን ሠነዶች በመመርመር ተከሳሾች የወንጀሉን ማቋቋሚያ የኾኑትን ፍሬ ነገሮች የፈፀሙ ስለመኾኑ ዐቃቤ ሕግ ባቀረባቸው የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች አረጋግጦ ጥፋተኛ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

የወንጀል ሕጉ ዓላማ አጥፊን በጥፋቱ ልክ በመቅጣት ከጥፋቱ እንዲማር እና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች ለመፈፀም የሚያስቡትን ማስጠንቀቅ በመኾኑ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት ምክንያት በማድረግ ከማረማያ ቤት ወጥተው በማምለጣቸው የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2ዐዐ7 አንቀጽ 6 መሠረት ብር 14ዐ ሺህ ብር እንዲከፍሉ በማለት ጥቅምት ዐ2/2ዐ17 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሣኔ አስተላልፎባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ምርመራውን ያጣራው ፖሊስ ተከሳሾችን በማፈላለግ ይዞ ለባሕር ዳር ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ እና ማረሚያ ቤቱም የእስራት ቅጣቱን እንዲያስፈፅም፤ የፍትህ ቢሮ የወንጀል ዐቃቤ ህግ የተወሰነውን ገንዘብ ተከታትሎ እንዲያስከፍል በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም ሦስተኛ ተከሳሽ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምንትዋብ እጅ መንሻ፣ የሩቅ ዘመን ማስታወሻ”
Next articleኢትዮጵያ ከታንዛንያ ጋር ዛሬ ትጫወታለች።