
ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከደም ግባት ያማረው ደም ግባት የተቸራቸው፣ ከብልሃትም የተወደደው ብልሃት የተሰጣቸው፣ ዘመን የተባረከላቸው፣ ታሪክ ያከበራቸው ንግሥት እጅ ነስተውባታል፤ የወርቁን መቀነት አውልቀው ወገባቸውን በሻሽ አጥብቀው ሱባኤ ገብተውባታል በቁስቋም፡፡ ይህች ስፍራ የሩቅ ዘመን ማስታወሻ፣ የሊቃውንቱ መዳረሻ ናት፡፡ የደጋጎቹ መማጸኛ፣ የብሩካኑ መጽናኛ ኾና አገልግላለች አሁንም እያገለገለች ነው፡፡
በተዋበች ሀገር ምንትዋብ ነገሡባት፤ በተዋበው ዙፋን ምንትዋብ ተቀመጡበት፤ የተዋበውን ዘውድ ምንትዋብ ደፉት፣ የተዋበውን በትረ መንግሥት ምንትዋብ ጨበጡት፤ የተቀደሰውን ቅበዓ ቅዱስ ምንትዋብ ተቀቡት፤ በተዋበው ቤተ መንግሥት በአስፈሪ ግርማ ምንትዋብ ኖሩበት፤ የተዋበውንም ቤተ መንግሥት ምን ትዋብ አሠሩት፤ የተቀደሰችውን ሀገር ምንትዋብ አሥተዳደሯት፤ በቃል ኪዳን ተቀብለው በቃል ኪዳን ጠበቋት፤ በቃል ኪዳንም ለልጅ ልጆቻቸው አስተላለፏት፡፡
ስምን መላዕክ ያወጠዋል ይሉት ግብር ተገለጠባቸው፤ ከዘመን ዘመን የማይደበዝዝ ግርማ ተሰጣቸው፤ ዘመናት ሲያልፉ የማይኮሰምን የሰው ፍቅር ተቸራቸው፡፡ ተውበው ተወልደው፣ ተውበው ኖረዋል፤ ከእነ ክብራቸውም አልፈዋልና ትውልድ በፍቅር ይጠራቸዋል፡፡
ገና በማለዳው በስም የከበሩት፣ በሥነ ምግባር የታደሉት፣ በግርማ የሚያስፈሩት፣ አያሌ ታሪኮችን የሠሩት እመቤት መቃብር ስማቸውን ሊያጠፋው አልተቻለውም፡፡ ይልቅስ ከመቃብር በላይ ይወደሳሉ፣ ከመቃብር በላይ ይሞገሳሉ እንጂ፡፡ በአማረው ዙፋን ላይ ተቀምጠው፣ በአልማዝ ባጌጠው ካባ ተንቆጥቁጠው፣ እጹብ የሚያሰኘውን በትረ መንግሥት ጨብጠው፣ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ከበዋቸው፣ እልፍ በቀኝ፣ እልፍ በግራ፣ እልፍ በኋላ፣ እልፍ በፊት እጅ እየነሳላቸው፤ ካማረው ቤተ መንግሥት በወጡ ጊዜ ለእግራቸው መረጋገጫ የወርቅ ምንጣፍ እየተዘረጋላቸው፣ ለክብራቸው እልል እየተባለላቸው፣ በእንቁ ያጌጠ ሰረገላ እየተዘጋጀላቸው በከፍታ ኖረዋል እቴጌ ምንትዋብ፡፡
እቴጌዋ በአልማዝ ማጌጡ፣ በእንቁ መንቆጥቆጡ፣ በአስፈሪ ዙፋን መቀመጡ፣ እጹብ የሚያሰኝ በትረ መንግሥት መጨበጡ አኩርቷቸው፣ አስመክቷቸው፣ ዘመናቸውን በደስታ እና በፌሽታ ብቻ አላሳለፉም፡፡ ይልቅስ ስማቸው የሚታወስበትን፣ ክብራቸው የሚነገርበትን፣ ዘመናቸው የሚዘከርበትን ታላቅ ታሪክ ሠሩ፤ ሀገራቸውን ዘለግ ላሉ ዓመታት በብልሃት፣ በታማኝነት፣ በጀግንነት መሩ እንጂ፡፡
እንደ ስማቸው ታሪካቸው እና ደም ግባታቸውም የተዋበ ነው፡፡ በሴት ስም በምትጠራው ጥንታዊት ሀገር ኢትዮጵያ ትናንት ላይ ቆመው ዛሬ እና ነገን የሚተነብዩ ትንቢተኛ፣ የማይቻል የሚመስለውን የሚችሉ ጥበበኛ፣ የሴት ነገሥታት ስም በተጠቀሰ ቁጥር የእርሳቸው ስምም ላቅ ብሎ የሚነሳ ብልሀተኛ ንግሥት ናቸው፡፡ ከዓላማቸው ሸብረክ የማያውቁ፣ በጥበብ እና በብልሃት የተራቀቁ፣ ጥበብን እና ዕውቀትን በትውልድ ልብ ላይ ያፈለቁ እመቤት ናቸው ይሏቸዋል እቴጌ ምንትዋብን፡፡
ተክለጻድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ በተሰኘው መጽሐፋቸው እቴጌ ምንትዋብ ኀይለኛ ብልህ፣ ሥልጣናቸው የገነነ ነበር ብለው ጽፈዋል፡፡ እኒህ ብልህ ንግሥት በብልሃት ሀገራቸውን መርተዋል፡፡
ታምራት ወርቁ “የመማጸኛ ከተማ” በተሰኘው መጽሐፋቸው በጎንደር ዘመን ስማቸውን በወርቅ ያስጻፉ ታሪካዊት ሴት ናቸው፤ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ አሻራ ትተው ያለፉ ንቁ፣ ኀይለኛ፣ ተራማጅ እና ጠንካራ መንፈሳዊት ሴት ነበሩ ብለዋቸዋል፡፡ የመሲህ ሰገድ በካፋ ባለቤት፣ የብርሃን ሰገድ ኢያሱ እናት፣ የአቤቶ ኢዮአስ አያት፣ የጎንደር እመቤት፣ የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት፣ የጥበብ እናት ናቸው እቴጌ ምንትዋብ፡፡ እንደ እርሳቸው በዙፋን ያማረ፣ እንደእርሳቸው በዙፋን የተከበረ፣ እንደ እርሳቸውም ዘለግ ላሉ ዓመታት በዙፋን የኖረ ከየት ይገኛል ይሏቸዋል፡፡ የንግሥተ ነገሥታት ዘመናቸው ከባለቤታቸው መሲህ ሰገድ አጼ በካፋ ጀምሮ እስከ ልጅ ልጃቸው አቤቶ ኢዮአስ ይዘልቃልና፡፡
አሰግድ ተስፋዬ “ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ” በሚለው መጽሐፋቸው ታላቋ ንጉሥት እቴጌ ምንትዋብ በዙፋን ስማቸው ብርሃን ሞገስ ተሰኝተው ለንግሥትነት የሚያበቃውን የክብር ልብስ የለበሱ፣ የወርቅ አክሊል የጫኑ ንግሥተ ነገሥታት የተባሉ መኾናቸውን ጽፈዋል፡፡ እቴጌዋ ለ47 ዓመታት በዙፋን ተቀምጠው ሀገራቸውን ያሥተዳደሩ ብቸኛ መሪ ያደርጋቸዋል ይሏቸዋል፡፡
ንግሥቷ ውበታቸው ያማረ፣ አስታዋይነታቸው የሰመረ፣ ክብራቸው ከፍ ከፍ ያለ ነበርና ንጉሥ እና ንግሥት ማንገስ፣ ጥፋተኛን መውቀስ፣ ከጥፋቱ መመለስ እና ጀግናን ማወደስ የሚያውቁበት ጎንደሬዎች እንዲህ ሲሉ ተቀኙላቸው አሉ፡፡ “አሁን ወጣች ጀምበር ተደብቃ ነበር ደስ ይበልህ ጎንደር” እነኛ ብልሆች በስም ምንትዋብ ተብለው፣ በምግባር አምረው የመጡትን ንግሥት ከጀምበር ጋር መሰሏቸው፤ የደስታ ማብሰሪያ አደረጓቸው፡፡ ተደብቀው የኖሩ፣ እንደ ጀንበር ያበሩ ናቸው አሏቸው፡፡
እቴጌ ምንትዋብ በዘመናቸው ሀገር በማሥተዳደር፣ የተንገጫገጨውን በማደላደል፣ ደብር በመደበር፣ ገዳም በመገደም፣ አብያተ መንግሥታትን በማሳነጽ፣ ትውልድን በጥበብ በመቅረጽ፣ ሥልጣኔን በማስፋት አያሌ ታሪኮችን ሠርተዋል፡፡ በተዋበው የጎንደር አብያተመንግሥታት ቅጥር ውስጥ እጹብ የሚያሰኝ ቤተ መንግሥት አሠርተዋል፡፡ ከዋናው ቤተ መንግሥት ግቢ ባሻገር በሚገኝ የተዋበ ስፍራም ሌላ ቤተ መንግሥት እና የረቀቀች ቤተክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ቀጭን ፈታዮች እና ወይዛዝርት ግንብ የሚባል በእርሳቸው አማካኝነት የተሠራ ውብ አሻራም አላቸው፡፡ በቀጭን ፈታዮች እና ወይዛዝርት ግንብ ውስጥ ወይዛዝርቱን ሙያ ያስተምሩበት ነበር ይባላል፡፡ ይህም ሕንፃ ዶሮ 12 ብልት ተወጥቶላት፣ በቅመም ተከሽና ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበችበት ነው ይባላል፡፡
“አለው አለው እና ሲዘፈን በጎንደር
ንቅሳት ጌጥ እንጂ መች መለያ ነበር” እንዳለች ድምጸ መረዋዋ ጥርስን በንቅሳት የማስዋብ፣ ከውበት ላይ ውበት የመደራረብ ጥበብ እና አጊያጊያጥ የተጀመረውም በእኒሁ ንግሥት ዘመን እንደኾነ ይነገራል፡፡ በዘመናቸው አያሌ አዳዲስ ነገሮችን ያመጡት እመቤት ባሕል፣ ታሪክ እና እሴት በተነሳ ቁጥር እርሳቸውም ጎላ ብለው ይነሳሉ፡፡
እቴጌ ምንትዋብ ዙፋን ላይ ሲቀመጡ ኩሩ፣ ጀግና እና አስተዋይ ንግሥት፣ ወደ ደብር ሲያቀኑ ፍሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው እመቤት፣ ወደ እልፍኝ ሲገቡ ሴትነትን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በሙያ የተራቀቁ ሴት ናቸው፡፡ ሁሉን የተቸራቸው እመቤት፣ ሁሉ ያላቸው ንግሥት ናቸው ይሏቸዋል፡፡ እቴጌዋ ለመቀመጫቸው አብያተ መንግሥታትን፣ ለክብራቸው መገለጫ ያማሩ እልፍኞችን፣ ለወይዛዝርቱ መማሪያ የተዋቡ ኪነ ሕንጻዎችን ብቻ አይደለም ያሠሩት፡፡ አድባራትን ማስደበር፣ ገዳማትን ማስገደምም ተክነውበታል እንጂ፡፡ በመናገሻዋ ከተማ በጎንደር ብቻ ሳይኾን በጣና እና በሌሎች አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ በዚያች በነገሡባት፣ በክብር እና በግርማ በዙፋን ላይ በኖሩባት፣ ባማረ ቤተ መንግሥት በተመላለሱባት፣ እልፍ በኋላቸው፣ እልፍ በግራቸው፣ እልፍ በቀኛቸው ባሰለፉባት፣ ዘመናትን አልፎ የሚያስጠራ ታሪክ በሠሩባት በመናገሻዋ ከተማ ጎንደር ያሠሯት የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም፤ አሻራቸውን እና ረቂቅ ጥበባቸው እየነገረች ትኖራለች፡፡
አሰግድ ስለ ደብረ ጸሐይ ቁስቋም እና ስለ ቤተመንግሥታቸው ሲጽፉ “ ይህ ታሪካዊ ሥፍራ ለቀሃ ወንዝ የሚገብሩት የዛኒ ገደል እና አሙዛ ዥረቶች መሐል የሚገኝ ነው፡፡ ዛኒ ማለት ደጀን ማለት ነው፡፡ ይህ አውደ ግቢ የእቴጌ ምንትዋብን የጣት ቀለበት ጨምሮ አንድ ሺህ ወቄት ከአንድ ቀለበት ወርቅ ወጥቶበት በቀን አንድ ሺህ ሠራተኞች አምስት መቶ ሠሪ፣ አምስት መቶ (አነዋሪ) አስተካካይ እየኾኑ የሠሩት ነው፡፡ ግቢዎቹም ከጥንት ጀምሮ የቤተክርስቲያኗ ግቢ እና የሺህ ወቄት ግቢ ተብለው ይጠራሉ” ብለዋል፡፡ ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በተሰኘው መጽሐፋቸው ደግሞ አንድ ሺህ ሠሪ አምስት መቶ አስተካካይ ኾነው ይሠሯት ነበር ብለዋል፡፡ በቀደመው ዘመን “ሺህ ሰሪ ሺህ አነዋሪ” እያሉ አበው እንደሚጠሩት ማለት ነው፡፡
ተክለጻድቅም እቴጌ ምንትዋብ እስከዛሬ ድረስ የሚያስደንቀውን የቁስቋምን ቤተክርስቲያን በዘመናቸው የጣት ቀለበታቸውን ጭምር ሰጥተው ማሠራታቸውን፣ ሥራውም ሲያልቅ ከፍ ባለ ክብረ በዓል እንደተከበረ ጽፈዋል፡፡ የኅዳር ቁስቋም በምትውልበት ቀን እቴጌዋ የቁስቋምን፣ የሌሎች አድባራትን እና ገዳማትን ሊቃውንት እየጠሩ ግብር ያበሉ እንደነበርም ተጽፏል፡፡
ደብረ ፀሐይ ቁስቋም በግብጽ ሀገር ከምትገኘዋ የማርያም ገዳም ከተገደመበት ቦታ ስያሜዋ የተወሰደ ነው ይባላል፡፡ እቴጌዋ ይህችን ያማረች እና የተዋበች ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሲያሠሩ እንቅልፍ ትተው እንደነበርም ይነገራል፡፡ የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን ቀዳሽ እና ታሪክ ነቃሽ ቀሳውስት እንደሚሉት ቤተክርስቲያኗ በ1733 ዓ.ም በዝነኛዋ ንግሥት እቴጌ ምንትዋብ አማካኝነት ነው የታነጸችው፡፡ አሰግድ ተስፋዬም ሕንጻ ቤተክርስቲያኗ በ1725 ዓ.ም ጀምሮ መታነጽ እንደጀመረች ጽፈዋል፡፡
ድንግል ማርያም በስደቷ ዘመን በግብጽ በቁስቋም ኖራለች፡፡ እቴጌ ምንትዋብም የተሰደደችውን፣ ከፍጥረታት ሁሉ የላቀችውን እመቤት መታሰቢያ ይኾን ዘንድ ቁስቋም ማርያምን አሳነጹ ይላሉ አበው፡፡ እቴጌዋ ወረኃ ጽጌ ስትፈጸም ለክብረ በዓል ወደ ቀድሞዋ ምሥር ወደ አሁኑ ግብጽ የሚሄዱ አማኞችን ከእንግልት ለማዳን ያሳነጿት፣ ዳግማዊት ቁስቋም ትኾን ዘንድም የመረጧት ናትም የሚሉም አሉ፡፡ እቴጌ የእመቤታቸውን ታሪክ ለማስታወስ አምላካቸውን ለማመስገኛነት እና ለመማጸኛ ያስገኙቧት ናትም ይሏታል፡፡
ይህች ያማረች እና የተዋበች ቤተ መቅደስ ከ44ቱ የጎንደር አብያተክርስቲያናት መካከል አንደኛዋ ናት፡፡ ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በሚለው መጽሐፋቸው በቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን በርካታ የእንቁላል ግንቦች አብረው መገንባታቸውን ጽፈዋል፡፡ የእንቁላል ግንቦችም የባሕታውያን መኖሪያ፣ የእንግዶች ማረፊያ፣ የምግብ ቤት አዳረሽ፣ የእቴጌዋ የጸሎት ቤት እና ሌሎች ያማሩ ኪነ ሕንጻዎች ናቸው፡፡ ይህች ያማረች ቤተ መቅደስ ጣሪያዋ በወርቅ እና በብር ተለብጣ እንደተሠራች ይነገራል፡፡ ጣሪያውም ተሠርቶ በተፈጸመ ጊዜ በቀይ ግምጃ ተሸብቦ ነበር ይባላል፡፡ ይህች የተዋበች ቤተ ክርስቲያን በኖራ፣ በሥንዴ ዱቄት፣ በእንቁላል፣ ሙጫ እና ጥሬ ጨው አምራ እንደተገነባች ይነገራል፡፡ ወይራ፣ ግማርዳ፣ ደንበቃ እና ዝግባ ደግሞ ለቤተ መቅደሱ መሥሪያነት የተመረጡ እንጨቶች ናቸው፡፡ እቴጌዋ ለቤተክርስቲያኗ ቀሳውስትን፣ ደባትራትን እና ጠባቆችን እንደመደቡላቸውም ይነገራል፡፡
ዘመናት አለፉ፤ ዘመናትም ተተኩ፤ መሐዲስቶች በጀግኖቹ ሥፍራ ወረራ ፈጽመው አብያተክርስቲያናትን አቃጠሉ፤ ገዳማትን በእሳት አነደዱ፤ ቀሳውስትን እና መነኮሳትን ገደሉ፡፡ በዚህም ዘመን ቃጠሎ ከደረሳባቸው የጎንደር አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት መካከል ደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም አንደኛዋ ናት፡፡ ድርቡሾች ዘርፈዋታል፤ አውድመዋታልም፡፡ የረቀቀችውን አሻራ በእጅጉ አጎሳቁለዋታል፡፡ ዳሩ የእቴጌን አሻራዎች፣ የገዘፉ ታሪኮች እና ጥበቦችን ማጥፋት አልተቻላቸውም፡፡ ልጆቿ እንደገና ሠርተዋት፣ ነገሥታቱ አስውበዋት ታሪኳ ቀጠለ፡፡ ቤተ መቅደሷም እንደገና ተዋበች፡፡ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ውብ ኾና መታደሷም ይነገራል፡፡
ይህች ውብ ቤተክርስቲያን ታሪኳን እንደጠበቀች በዚህ ዘመንም ታድሳለች፡፡ በዚያች ያማረች ቤተክርስቲያን ውስጥ የበዙ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከፈረስ ቆዳ የተጻፈ ነገረ ማርያም፣ ገድለ ሰማዕታት፣ ድጓ፣ መስቀሎች፣ ጽዋዎች፣ የእቴጌዋ ማረፊያ አልጋቸው፣ ማንበቢያ አትሮንሳቸው እና ሌሎች የበዙ ቅርሶች ይገኙባታል፡፡ ወርሐ ኅዳር ብቶ በዓለ ቁስቋም በደረሰ ጊዜ በጎንደር የሚገኙ አማኞች በሰማይ ማርያምን፣ በምድር ምንትዋብን እያሰቡ ወደ ቁስቋም ይጓዛሉ፡፡ የቁስቋም አጸድ ነጫጭ በለበሱ አማኞች ይሞላል፡፡
ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ እና የጦር አበጋዞች፣ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ አጊጠው ወደ ቁስቋም ማርያም በክብር ያቀኑ ነበር፡፡ ዛሬም የነገሥታቱ የልጅ ልጆች፣ የነገሥታቱ ታሪክ ጠባቂዎች እና የመናገሻዋ ከተማ ነዋሪዎች በዓለ ቁስቋም በደረሰች ጊዜ ከአራቱም ንፍቅ እየወጡ ወደ ቁስቋም ይገሰግሳሉ፡፡ በዓለ ቁስቋምን ለማክበር የወደዱ ኢትዮጵያውያንም ወደ ቁስቋም ይመጣሉ፡፡ የማርያምን ስደት እያሳቡ ይሠባሠባሉ፡፡ እነሆ ቁስቋም ደርሳለች፤ ነጭ የለበሱ አማኞች በቁስቋም አጸድ ሥር ተሠባሥበዋል፡፡ የጌታቸውን እናት የማርያምን፣ የንግሥታቸውን የምንትዋብን ነገር እያሰቡ በዓሉን ያከብራሉ፤ በደስታ መጥተው፣ በደስታ ለዓመት ቀጠሮ ይዘው፣ አደራውንም ለአምላካቸው ሰጥተው በደስታ ይመለሳሉ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!