የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-ወጥ ስደትን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

49

አዲስ አበባ: ኅዳር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለፍልሰት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት የሚያስችል ሁለተኛው ምዕራፍ የትብብር እና የአጋርነት መድረክ ተካሂዷል። ትብብር እና አጋርነቱ የተካሄደው ኮምፓስ (COMPASS) በተሰኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ዩ ኤን ማይግራንትስ በኢትዮጵያ ፕሮግራም እና በኔዘርላንድ መንግሥት ነው።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ መንግሥት አምባሳደር ክሪስቲን ፒሬኔ ባደረጉት ንግግር ስደትን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ፤ የድንበር አሥተዳደር፣ የፍልሰት አሥተዳደር እና የመመለሻ አስፈላጊነትን በተመለከተ የኔዘርላንድስ መንግሥት በትኩረት የሚሠራባቸው ጉደዮች እንደኾኑ አንስተዋል። በ ኮምፓስ ውስጥ በስደተኞች ጥበቃ፣ በዳግም ውህደት ድጋፍ፣ የፍልሰት አሥተዳደርን ማጠናከር እና ሕገ-ወጥ የስደት ስጋቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት እየሠራባቸው ያሉ ጉዳዮች መኾናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞችን ተግዳሮቶች ለመፍታት ጠንካራ አቋም አሳይቷል ያሉት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉደይ ሚኒስትር ዲኤታ ሁሪያ አሊ መደበኛ ያልኾነ ስደትን ለማስቀረት እና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ መደበኛ እና ክብር ባለው መንገድ እንዲኾን ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በሕገ-ወጥ ስደት ዙሪያ ያለውን ተግዳሮት ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ብዙ የሚቀር ሥራ ቢኖርም በተጀመሩ ጥረቶች፤ የሥነ ልቦናና የክህሎት ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ከሳዑዲ አረቢያ፣ የመን፣ ታንዛኒያ እና ከሌሎች ሀገሮች ለሚመጡ ስደተኞች የመመለሻ ድጋፍ እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እየተሠራ መኾኑንም ነው ያመላከቱት። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ለኢትዮጵያ በተለያዩ የስደት ጉዳዮች ላይ ለሚያደርገው ድጋፍም ልዩ ምሥጋናም አቅርበዋል።

የአይ.ኦ.ኤም ተወካይ በኢትዮጵያ አቢባቱ ዋነ እንዳሉት የኮምፓስ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግሥት ስደትን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ፤ ጠንካራ ማኅበረሰቦችን ለመገንባት እና ለስደተኞች ብሩህ የወደፊት ተስፋ ለመስጠት እንሠራለን ነው ያሉት።

የተቋማቸውን ዋና ዓላማ የተናገሩት አቢባቱ የስደት ፈተናዎችን በመቀነስ ተስፋ እና ዕድል መስጠት፤ ለችግር የተጋለጡ ስደተኞች ሕይወታቸውን መልሰው እንድገነቡ፣ ወደ ማኅበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ እና እንዲበለጽጉ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች በማሟላት እንደግፋለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የባሕር ዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
Next article“የምንትዋብ እጅ መንሻ፣ የሩቅ ዘመን ማስታወሻ”