
ባሕር ዳር: ኅዳር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ ጠዋት ባሕር ዳር ከተማ ገብተዋል። ፊልድ ማርሻሉ በክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታዎች እና የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ሥራዎች ዙሪያ ከክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። የውይይቱ ዓላማም የክልሉ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ፣ ሕዝቡም የተረጋጋ ኑሮውን እንዲመራ እና ሙሉ አቅሙን በልማት ሥራዎች ላይ እንዲያውል ለማድረግ ያለመ ነው።
ለዚህም የጸጥታ ኃይሉ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ በውይይቱ ተነስቷል። ሰላም ወዳዱ የአማራ ሕዝብ ከጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት ሰላሙን የሚያደፈርሱ አካላትን መከላከል፣ ሰላምንም ማስፈን እንደሚገባው ተነስቷል።
ፊልድ ማርሻሉ በከሰዓት መርኃ ግብራቸው ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ከሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመኾን በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው። ፊልድ ማርሻሉ የባሕር ዳር ተጨማሪ የውበት ምንጭ የኾነውን የአባይ ድልድይ በመቀጠልም ግዙፉን የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ፣ የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት እና ሌሎችንም የልማት እንቅስቃሴዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!