የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አብሮነትን እና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

69

ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አብሮነትን እና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ከፍያለው ማለፉ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በአማራ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በአማራ ክልል በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበርም ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን አብሮነት በሚያጸና መልኩ እየተከበረ መምጣቱን የተናገሩት ኀላፊው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንም “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡ በዓሉ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚከበርም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር ዋናው ዓላማ እና የትኩረት አቅጣጫው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ማጽናትን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች የሚካሄዱ የፓናል ውይይቶች እና ሁነቶች አብሮነትን እና የሕዝቦች አንድነትን በሚያጸና መልኩ ይካሄዳሉ ነው ያሉት፡፡ በበዓሉ አከባበር ሂደት፣ በፌዴራሊዝም እና በሕገ መንግሥት አስተምህሮ ላይም ግንዛቤ እንደሚፈጠር ነው የተናገሩት፡፡ በበዓሉ የአማራ ሕዝብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የተጫወተውን እና እየተጫወተው ያለውን ሚና፣ ሕገ መንግሥትን በማክበር እና በማስከበር፣ ለሕግ የበላይነት መከበር ያለውን ጽኑ ዕምነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርበትን አውድ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል፡፡ በዓሉ አብሮነትን እና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸው እንዲከበር፣ ለፍትሕ እና ለነጻነት መረጋገጥ በጋራ ጠንክረው የሚሠሩበትን አውድ እንፈጥርበታለን ብለዋል፡፡ ፍትሕ፣ ነጻነት እና ሰላም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ክልሉ አሁን ካለበት ችግር የሚሻገርበት እና አብሮነትን የሚያጠናከርበት ውይይት በሁሉም ከተሞች ይደረጋል ብለዋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ እህታማማችነትን እና ወንድማማችነትን ማጽናት አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የጋራ ሀገር የኾነችው ኢትዮጵያ የምትገነባው በአብሮነት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለጋራ ብልጽግና እና ለጋራ ሰላም ሲሉ አብረው የሚተሳሰሩበት በዓል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በዓሉን ለማክበር በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሚመራ 13 አባላት ያሉት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ዐቢይ ኮሚቴው በሥሩ ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዳሉትም አስታውቀዋል፡፡ ኮሚቴዎቹ ለበዓሉ ስኬታማነት እና የሚፈለገውን ዓላማ ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ነው የተናገሩት፡፡

በክልል ደረጃ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአርጎባ ልዩ ወረዳ ኅዳር 8/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡ በአርጎባ በሚካሄደው በዓል የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የአጎራባች ክልል መሪዎች እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

በዓሉ ከውይይቶች ባሸገር በደም ልገሳ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና በሌሎች ሁነቶች እንደሚከበርም ገልጸዋል፡፡ በክልል ደረጃ የማጠቃለያ ዝግጅቱ ኅዳር 24/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድም አመላክተዋል፡፡ በተለይም በሕገ መንግሥት እና በፌዴራሊዝም ሥርዓት የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች 3 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ኅዳር 29/2017 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ለሚከበረው በዓል ክልሉን የሚወክል ልዑክ እንደሚሄድም ተናግረዋል፡፡ በዓሉ አብሮነት የሚጸናበት ኾኖ እንዲከበር ክልሉ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

በዓሉ የተሳካ፣ የደመቀ እና የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ ማኅበረሰቡ በውይይቶች እንዲሳተፍ እና ሰላሙን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሰላምን ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የሚፈለገው ዴሞክራሲ እንዲመጣ፣ ጠንካራ ሀገር እንዲገነባ እና አብሮነት እንዲጸና ማኅበረሰቡ የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከ156 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ጉድጓድ አጠናቅቆ ለከተማ አስተዳደሩ አስረከበ።
Next articleፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የባሕር ዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።