
አዲስ አበባ: ኅዳር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ)13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ ከኅዳር 10 እስከ 11/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የኮንፈረንሱን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ አዘጋጆቹ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በኮንፈረንሱ ከ22 እስከ 25 የሚደርሱ የዓለም ሀገራት እንደሚሳተፉ የገለጹት በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ያስሚን ወሀረቢ እስካሁን ከ110 በላይ ተሳታፊዎች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ከኢትዮጵያም ከ430 በላይ ላኪዎች፣ አምራቾች፣ ጥናት አቅራቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ሲሉ ሚኒስትር ድኤታዋ ገልጸዋል።
ኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ በጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ምርት እና ወጪ ንግድ ያላትን እምቅ ሃብት ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ያለው መኾኑንም ሚኒስትር ድኤታዋ ገልጸውዋል።
ኮንፈረንሱ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እና የገበያ መዳረሻ ሀገራትን ለማስፋፋት ያግዛል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!