
ደሴ፡ ኅዳር 6/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ መለስተኛ ቀዶ ጥገና ለመስጠት ማስፋፊያ እየተገነባላቸው ካሉ 117 ጤና ጣቢያዎች መካከል 104ቱ መጠናቀቃቸውን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አሳውቋል፡፡
ወይዘሮ ትብለጥ ሞገሴ የኩታበር ወረዳ ነዋሪ ናት። በእናትነት ሕይወቷ ልጅን እስከማጣት የደረሰ ከባድ ፈተና ተጋፍጣለች። ሁለተኛ ልጇን የሕክምና አገልግሎት በፍጥነት ማግኘት ባለመቻሏ በሞት የተነጠቀችው ትብለጥ ሦሥተኛ ልጇን በኩታበር ጤና ጣቢያ በሰላም መገላገሏ አስደስቷታል።
“ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር በመቀረፉም ልጅ ወልጄ እንድስም አድርጎኛል” በማለት ስሜቷን ገልጻለች።
የኩታበር ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ነርስ ጀማል አንዳርጌ ከ60 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሠጠው ጤና ጣቢያው የመለስተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት በመጀመሩ በርካቶችን ከሞት ለመታደግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በሰባት ወረዳዎች የመለስተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ናቸው።
በክልሉ ለመለስተኛ ቀዶ ጥገና የህክምና አገልግሎት በ117 ጤና ጣቢያዎች ማስገንባት መጀመሩን የገለጹት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ከእነዚህም ውስጥ የ104ቱ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የጤናው ዘርፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በማሟላት የእናቶችን እና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ቢሮ ኀላፊው አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡- ሕይወት አስማማው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!