
ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2016 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ እና በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተምረው ከዩኒቨርሲቲዎቹ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ ሴት ተማሪዎችን ለማበረታታት የዕውቅና እና የሽልማት መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
ሽልማቱን የተቀበሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ እና በከፍተኛ ውጤት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሴት ተማሪዎች ሽልማቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ስኬት የበቁትም የሚያጋጥሙ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው በመሥራት እንደኾነ ነው ያብራሩት፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት እና ልምዳቸውን ያካፈሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ ምህረት አብርሃም ሴቶች ነገን የሚያልሙ፣ ለብልጭልጭ ነገር የማይታለሉ እና ራዕይ ያላቸው መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይንሸት ዘሪሁን ሴትነት በተፈጥሮ ሁሉንም ነገር አሟልቶ የተሰጠን ፀጋ ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች ይህንን ዕድል ተጠቅመውም በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ለስኬት መብቃት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ዛሬ ለዕውቅና እና ሽልማት የበቁ ተማሪዎች ዓላማቸውን ያሳኩ ከተማ አሥተዳደሩ የሚኮራባቸው ስለመኾናቸውም ነው የተናገሩት፡፡ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁትም ሥራ ፈጣሪ በመኾን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያገለግሉም አሳስበዋል፡፡
በዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከ3 ነጥብ 6 በላይ በኾነ ከፍተኛ ውጤት የተመረቁ 50 ተመራቂዎች ይገኙበታል። በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 30 ተማሪዎች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሠለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!