
አዲስ አበባ: ኅዳር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲኒያ ባንክ 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ 15ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን እያካሄደ ነው። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ዓለም ዓቀፋዊ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ጅኦ ፖለቲካዊ ቀውሶች እና ሀገራዊ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ግጭቶች ፈተና ቢኾኑም ይህን ተቋቁሞ በበርካታ የባንኩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር አዕምሮ በለጠ ተናግረዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ በተቀማጭ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል። 33 ነጥብ 97 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡም ተነግሯል። ይህ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 21 ነጥብ 43 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተነስቷል።
ብድር፣ ቅድመ ክፍያዎች እና ከወለድ ነጻ የተሰጡ ብድሮች ተካትተውበት 167 ነጥብ 74 ቢሊየን ብር መድረሱን አቶ አዕምሮ በለጠ ተናግረዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 14 ነጥብ 49 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው የተባለው። ከዚህ በተጨማሪም ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ማድረስ መቻሉን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ባንኩ በዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሬ 424 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱ ተጠቅሷል። ይህ አሃዝ ካለፈው የበጀት ዓመት ቅናሽ እንዳሳየ ነው የተነገረው። የውጭ ምንዛሬ ገቢውን ለማሳደግም ባንኩ ከዓለም አቀፉ የንግድ አጋሮች ጋር ግንኙነቱን ማጠናከር እና ዓለም ዓቀፍ ካርድ ተጠቃሚ ቁጥሮችን መጨመር ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ተብሏል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ 27 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ ገቢ ማግኘቱንም በጉባዔው ተነግሯል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ5 ቢሊዮን ብር እድገት እንዳሳየ አቶ አዕምሮ በለጠ ተናግረዋል።
ባንኩ ያልተጣራ ትርፍ 5 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር ማግኘቱንም የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በሪፖርቱ አሳውቋል። የግብር እና ሌሎች ወጭዎች ተቀናንሶም ለባለአክሲዮኖች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል ይፈጸማልም ነው የተባለው።
ከተመሠረተ 28 ዓመታት ያስቆጠረው አቢሲኒያ ባንክ በመላው ኢትዮጵያ 930 ቅርንጫፎች ከፍቶ እየሠራ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!